ሀዋሳ፡ ሕዳር 01/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በመንግሥትና በዩኒሴፍ ድጋፍ ከ3 መቶ 50 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የንፁህ መጠጥ ውሃ ግንባታ ፕሮጀክት እያከናወነ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በከምባታ ዞን የዶዮገና ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የንጹህ መጠጥ ዉሃ ፕሮጀክት ግንባታው ሲጠናቀቅ ከ50 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስለመሆኑም ተገልጿል::
አቶ ደገሎ ዱምቾና አቶ በላቸው ሴንደኖ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከምባታ ዞን የዶዮገና ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ናቸው::
በከተማው የውሃ መስመር ያለ ቢሆንም ረጅም ዓመታትን የንጹህ መጠጥ ዉሃ በማጣታቸው ምክንያት ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ሲጋለጡ ቆይተዋል::
ነዋሪዎቹ አክለውም የንፁህ መጠጥ ዉሃ ችግር ከአቅማችን በላይ በመሆኑ ተማሪዎችና ሴቶች የምንጭ ውሃ ፍለጋ ረጅም መንገድ በመጓዝ ለተለያዩ እንግልት ሲደረጉ መቆየታቸውንም ጠቁመዋል::
በአሁኑ ወቅት የከተማ አስተዳደሩ የነዋሪዎችን የረጅም ጊዜ የንፁህ መጠጥ ዉሃ ችግር ለመቅረፍ እየሰራ ባለው ስራ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል::
የዶዮገና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ግሩም ወልደማርያም እንደተናገሩት የከተማውን የንፁህ መጠጥ ዉሃ ችግር ለመቅረፍ ከተማ አስተዳደሩ በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል::
አሁን ላይ እየተስተዋለ ያለውን የከተማውን የንፁህ መጠጥ ችግር ለመቅረፍ የዋገባታ-ዶዮገና ከርሰ ምድር የንጹህ መጠጥ ዉሃ ስራ ተጠናቆ የመስመር ዝርጋታ እየተፋጠነ መሆኑን ገልጸዋል::
ለዉሃ ፕሮጀክት ግንባታ ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በመንግስት እና በዩኒሴፍ ግንባታ እየተከናወነ መሆኑንም አቶ ግሩም አመላክተዋል::
የከተማውን የውሃ ሽፋን ለማሳደግ እየተሠሩ ያሉ የፕሮጀክቶችን ግንባታ በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ከንቲባው ጠቅሰዋል::
ስራዎች በስድስት ወራት ተጠናቀቀው ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንደሚሰጡም ገልጸዋል::
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የዶዮገና ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎችን ጨምሮ የአጎራባች ቀበሌያትንም ተጠቃሚ እንደሚያደርግም አቶ ግሩም ገልጸዋል::
ዘጋቢ: በየነ ሰላሙ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የህብረተሰቡን የኑሮ ዘይቤ ሊያሻሽሉ የሚችሉ አሠራሮች ተዘርግተው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸው ተመላከተ
የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች ውጤታማ ለማድረግ የዘርፉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ሚና የላቀ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ገለፀ
ለወባ ወረርሽኝ ምክንያት የሚሆኑ አካባቢዎችን የማጽዳትና ፍሳሾችን የማስወገድ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የቦንጋ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ