በጎፋ ዞን 19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ለማክበር በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

በጎፋ ዞን 19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ለማክበር በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

በበዓሉ አከባበር ላይ ያተኮረ ለባለድርሻ አካላት በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ የጎፋ ዞን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ አበበች መርጊያ ተገኝተው፤ 19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በተደመረ አቅም አንድነትንና ሰላምን ለማጽናት በሚያስችል መልኩ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ለብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለብዝኃነት ዕውቅና ለመስጠት፣ እኩልነትን ለማስተናገድ፣ አንድነትንና ሰላምን ለማጽናት የበዓሉ መከበር ፋይዳው የላቀ መሆኑን አንስተዋል።

ለ19ኛ ጊዜ የሚከበረው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን “አገራዊ መግባባት ለሕብረ-ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ የሚከበር በመሆኑ በዞኑ የሚገኙ ባህል፣ ታሪክ፣ እሴትና የተፈጥሮ መስህብ የሚተዋውቁበት መድረክ መሆኑን ጠቁመዋል።

የፌደራሊዝም ጽንሰ ሀሳብ ላይ ሰነድ ያቀረቡት የዞኑ ምክር ቤት የህግ ፍትህና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ቦረና ቦኖ፤ ፌደራሊዝም ለኢትዮጵያ ህልውና መሠረት በመሆኑ ባለድርሻ አካላት ፌደራሊዝምን በሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

በዓሉ በክልሉ መከበሩ ትልቅ ዕድል መሆኑን ገልጸው ያሉ መልካም እሴቶችን በተደመረ አቅም አንድነትን ለማጠናከር ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልፀዋል።

የጎፋ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ድንበሩ ደርቤ፤ የበዓሉ መከበር በዞኑ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች ባህል፣ ታሪክና እሴቶችን የመጠበቅ፣ የማስተዋወቅና የመንከባከብ ሥራ ውጤታማ ለማድረግ የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል።

ያነጋገርናቸው የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፤ በዓሉ የአንድነት፣ የሰላም፣ የመቻቻል እንዲሁም የሕብረ-ብሔራዊነት ቀለም መገለጫ በመሆኑ በዓሉን በተሳካ ሁኔታ ለማክበር በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በየዓመቱ ኅዳር 29 ቀን የሚከበር መሆኑ ይታወቃል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን