በኃይለማሪያምና ሮማን ፋውንዴሽን አዘጋጅነት በደቡብ ኦሞ ዞን ያሉ የአርብቶ አደር ማህበረሰቦችን ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ውይይት በቱርሚ ከተማ እየተካሄደ ነው
ሀዋሳ፡ ጥቅምት 29/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በኃይለማሪያምና ሮማን ፋውንዴሽን አዘጋጅነት በደቡብ ኦሞ ዞን ያሉ የአርብቶ አደር ማህበረሰቦችን በግብርናና በእንስሳት ሀብት ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቱርሚ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩም የኢፌዲሪ የቀድሞ ቀዳማዊት እመቤት እና የኃይለማሪያምና ሮማን ፋውንዴሽን መሥራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬን ጨምሮ የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር ከፈተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የውይይቱ ዋና አላማ አርብቶ አደሩ በእጅ ያለውን የእንስሳት ሀብትን በአግባቡ እንዲጠቀምና የገበያ ትስስር መፈጠር እንዲሁም በአካባቢው ያሉ የውሃ አመራጮችን በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ፋውንዴሽኑ ከመንግሥትና ከአጋር ድርጀቶች ጋር በቅንጅት መስራት መሆኑ ተመልክቷል።
የኃይለማሪያምና ሮማን ፋውንዴሽን የግብርና የምግብ ዋስትና ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ፋላሃ፤ ፋውንዴሽኑ በኢትዮጵያ መንግሥት ህዝብ እንዲሁም ከአጋር አካላት ጋር በመሆን በኢትዮጵያና በምስራቅ አፍሪካ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ዘርፍ ብዙ በሆነ ሁኔታ ለማገልገልና በማህበረሰቡ ዘንድ የሚታዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በጋራ ለመቅረፍ ተስቦ የተቋቋመ የበጎ አድራጎት ድርጅት መሆኑን አብራርተዋል።
ድርጅቱም በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ዘርፎች እየሰራ ያለ ድርጅት ሲሆን በደቡብ ኦሞ ዞን በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም፣ በእንስሳት ሀብት ምርታማነት፣ በግብርናና በጎጂ ልማዳዊ ድርጊት አወጋገድ፣ በትምህርትና በጤና ዘርፎች በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን አቶ ተሰፋዬ ተናግረዋል።
ፋውንዴሽኑ ባለፉት ስድስት አመታት በእናቶችና ህጻናት ጤናና ስነ-ምግብ፣ በትምህርት ዘርፍ በተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም፣ በትምህርት መሠረተ ልማት ማሟላት እንዲሁም የሴቶች ኢኮኖሚያዊ አቅም በማጎልበት በኩል በማህበር በማደራጀት ገቢ ማስገኛ ተግባራት ላይ እንዲሳተፉና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን የግብርና የምግብ ዋስትና ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ፋላሃ ተናግረዋል።
የፋውንዴሽኑ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ፤ በዞኑ ፋውንዴሽኑ እያከናወነ ያለውን ተግባራትና በቀጣይ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ በግብርናው ልማት ሥራዎች ውጤት ለመምጣት በትብብር እንሰራለን ሲሉ ለተሳታፊዎች ገለጸዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ሀላፊ አቶ ታደለ ጋያ፤ በዞኑ በርካታ ግብረሰናይ ድርጅቶች በተለያዩ ልማት ሥራዎች ላይ እየተሳተፉ መሆኑን ጠቁመው በዞኑ ያሉ አርብቶ አደር ማህበረሰቦች ከተለመደው እርሻ ዘይቤ በመውጣት ዘመናዊ የግብርና ግብአቶችን በመጠቀም የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ የተሻለ የአመጋገብ ሥነ-ሥርዓት ለመፈጠር ከኃይለማሪያምና ሮማን ፋውንዴሽን እንዲሁም ከሌሎች አጋር ድርጀቶች ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።
የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ምንላረገው አዲሱ በመድረኩ ባቀረቡት ማብራሪያ፤ በዞኑ ያለውን ዕምቅ የእንስሳትና የተፈጥሮ ሀብትን ለማልማት የግብርና ማሰልጠኛ ተቋማት ብቁና ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ በእንሰሳት እርባታ፣ በመስኖ ልማትና በተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ላይ ከፋውንዴሽኑና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት የዞኑ መንግሥት በልዩ ሁኔታ ይሰራል ብለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም በዞኑ በመንግስትና በተለያዩ ድርጅቶች በእንስሳት እርባታ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤና እና በእናቶችና ህፃናት ላይ በሚፈፀሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና በሌሎችም ጉዳዮች የሚያከናውኑት ተግባራት መኖራቸውን ጠቁመው በእነዚህም ተግባራት ህዝቡ የሚፈለገውን ያህል ወጤት አለማግኘቱን አንስተዋል።
በቀጣይም በደቡብ ኦሞ ዞን በሚገኙ አርብቶ አደር ማህበረሰብ ዘንድ የሚታዩ የምግብ ዋስትና ጉድለት ለማሟላት፣ በግብርናው ዘርፍ ከሚመለከታቸው መንግታዊና መንግታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በትብብር በመሥራት የተሻለ ለውጥ ለመምጣት የውይይት መድረክ ማስፈለጉን ከፋውንዴሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ዘጋቢ፡ ጄታ ታገሠ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
የምግብ ዋስትና ዘላቂነትን ለማረጋገጥ የሌማት ትሩፋት ስራዎችን ከስራ እድል ፈጠራ ጋር በጥምረት እየተሰራ ነው – የጋሞ ዞን ግብርና መምሪያ
ወጥ የሆነ ሀገራዊ አንድነትና እሳቤ ኖሮን ህዝቡን አቀናጅተን እንድንመራ የሚያስችል ስልጠና አግኝተናል ሲሉ በኣሪ ዞን 3ኛ ዙር የመካከለኛ ሰልጠኝ አመራሮች ገለፁ
የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ለሀገራዊ ዕድገት የሚኖረው ፋይዳ የጎላ በመሆኑ ተቋማት ትክክለኛ እና ጥራት ያላቸውን መረጃዎችን በማደራጀት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ተጠየቀ