በመደበኛና በተሻሻለ የግብርና ቴክኖሎጅ በመታገዝ በሰሩት የመኸር እርሻ ከአምናው የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ በኮንታ ዞን የኤላ ሀንቻኖ አንዳንድ አርሶ አደሮች ተናገሩ

ዘንድሮ ከ3 ሺህ 4መቶ በላይ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በመኸር ከተሸፈነው 53 ሺህ 5 መቶ በላይ ኩንታል ምርት እንደሚሰበሰብ የወረዳው ግብርና አካባቢ ጥበቃና ህብረት ሥራ ጽ/ቤት አስታወቀ።

አርሶ አደር ድናቶ ቦጋሞና ብራሞ መንሳ መሬትን በሚገባ አለስልሶ በማረስና ወቅቱን የጠበቀ የአረም ክትትል ማድረጋቸው እንዲሁም በግብርና ቴክኖሎጅ በመታገዝ ስንዴንና ባቄላን በመዝራት በአሁኑ ወቅት የማሳ ላይ ሰብላቸው የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል።

አካባቢው ለስንዴና ለባቄላ ምርት ምቹ በመሆኑ በኩታ ገጠም የግብርና ዘዴ አምና በሄክታር ስንዴ እስከ ሠላሳ ኩንታል ባቄላም እስከ ሃያ አምስት ኩንታል ማገኘት መቻላቸው ጠንክረው እንዲሰሩ እንዳነሳሳቸው አክለዋል።

አርሶ አደር ተረፈ ጦናና መሠለች ማሞ በኩታ ገጠም የእርሻ ዘዴ በመታገዝ ከሦስት ሄክታር በላይ ማሳ በስንዴ እያለሙ ሲሆን ከአምናው የተሻለ ምርት እንደሚያገኙና ለዚሁም የግብርና ባለሙያ እገዛ ትልቁን ቦታ ይይዛል ብለዋል።

ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብሉ ጫና ቢፈጥርም ማሳቸውን በምገባ ክትትል እያደረጉ በመሆናቸው በምርታማነቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሌለው ተናግረዋል።

የቀበሌ ግብርና ባለሙያ አቶ ወንድማገኝ ወርቁ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግና የአርሶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል በክህሎት ስልጠና የተደገፈው የተቀናጀ ተግባር አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ህወታቸውን እየለወጠ መሆኑን የገለፁት የዘንድሮ ኩታ ገጠም የስንዴ ምርት ለማዕከላዊ ገበያ እንደሚቀርብ ተናግረዋል።

የወረዳው ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ሥራ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተመስገን አበበ በመደበኛና በሙሉ ፓኬጅ 3 ሺህ 4 መቶ 33 ሄክታር ለማልማት ታቅዶ 3 ሺህ 4 መቶ 30 ሄክታር መሬት የለማ ሲሆን 53 ሺህ 5 መቶ 80 ኩንታል ምርት ይሰበሰባል ብለዋል።

ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ተከስቶ ችግር የፈጠረ ቢሆንም ለአርሶ አደሩ የተለየ ሙያዊ ድጋፍና ዕገዛ በማድረግ አሁን የደረሱ ሰብሎች በቤተሰብ ጉልበትና በደቦ የመሰብሰብ እንዲሁም እየደረሱ ያሉ ሰብሉች በአየር ፀባይ ለውጥ በሚከሰቱ በሽታዎች እንዳይጠቁ የክትትልና የቁጥጥር ሥራ እተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ አብዮት እሸቱ – ከዋካ ጣቢያችን