በሲዳማ ክልል ለተገኘው ሰላም የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ነበር – ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ
ሀዋሳ፡ ጥቅምት 28/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሲዳማ ክልል ለተገኘው ሰላም የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ እንደነበር የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ፡፡
የሲዳማ ክልል የሰላምና ፀጥታ ኮንፈረንስ በሀዋሳ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ፤ በሲዳማ ክልል ባለፉት አመታት ለሰፈነው ሰላም የህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ ቀዳሚ ሚና ነበረው ብለዋል።
ሰላም የሁሉም መልካም ነገር መግቢያ ቁልፍ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ሁሉም አካባቢውን መጠበቅ ከቻለ የጠቅላላውን ህብረተሰብ ሰላም ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል።
የሲዳማ ክልል የራሱን ሰላም በመጠበቅ ለሀገራዊ ሰላም መጠበቅ አወንታዊ ሚና እየተጫወተ መሆኑም ተመላክቷል።
በክልሉ በርካታ የፀጥታ ተቋማት ግንባታ በስፋት ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን ሀሳቡ የመንግሥት ቢሆንም ተግባሩን የፈፀመው ህብረተሰቡ በመሆኑ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።
የፀጥታ ጥበቃ ስራዎችን በቴክኖሎጂ ለማስደገፍ ጥረት የተደረገ ሲሆን የተሻለ ልምድ ካላቸው ሀገራትም ቦታው ድረስ በመሄድ ልምድ ተቀምሯል ተብሏል።
ሰላም እጃችን ላይ ማቆየት የምንችለው ሰላምን መንከባከብ ስንችል ብቻ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለሰላም ሁሌም በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል።
የሰላም ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ አቶ ቸሩጌታ ገነነ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት እንደአሉት፤ በሲዳማ ክልል የሰፈነው ሰላምና ፀጥታ ለሀገር አቀፍ ምሳሌ መሆን የሚችል ነው።
በሲዳማ ክልል ለተገኘው አመርቂ ውጤት መንግሥት ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት በሰራቸው ስራዎች ስለመሆኑ የሰላም ሚኒስቴር ይገነዘባል ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው፤ የህብረተሰቡ የዳበረ የሰላም እሴት ከሌሎች ህዝቦች ጋር በጋራ በፍቅር የመኖር መልካም ልምድ ውጤት ነው ብለዋል።
ህብረተሰቡን በማሳተፍ የተሰሩ የተቋማት ግንባታም ሌላው አርዓያ የሚሆን ተግባር ነው ብለዋል።
የሲዳማ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሀላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቴዎስ በበኩላቸው፤ ለጋራ ሰላም መጠበቅ የጋራ ጥረት ይጠይቃል ብለው ይሄንም ማድረግ በመቻሉ ተጨባጭ ለውጥ በክልሉ መመዝገቡን ተናግረዋል።
ከአጎራባች አካባቢ ክልሎች እና ዞኖች ጋር በጋራ ጉዳዮች ዙሪያ በቅርበት እየተሰራ በመሆኑ የሚፈጠሩ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ መፍታት ስለመቻሉም አንስተዋል።
በመድረኩ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ፣ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ከበደ፣ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሀላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቴዎስ፣ ከመላው ኢትዮጵያ የተጋበዙ የሰላምና ፀጥታ አካላት፣ የመከላከያና የፖሊስ ሰራዊት አባላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ባለድርሻዎች እየተሳተፉ ነው።
ዘጋቢ: ጀማል የሱፍ
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ