ሀዋሳ፡ ጥቅምት 27/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በልዩ ወረዳዉ ባለፉት ዓመታት ያጋጠመውን የትምህርት ጥራት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በዘርፉ ባለድርሻ አካላት በጋራ እየተሰራ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ትምህርት ፅ/ቤት አስታውቋል።
በቀቤና ልዩ ወረዳ የቀቤና ሁለተኛ ደረጃ እና የሀሰን ዑንጃሞ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች መካከል ተማሪ ሰባዉዲን ታጁ፣ ሀስና አብድልከሪም፣ ሀዉለት ሀሰን እና ተማሪ አንዋር ሙባረክ በሰጡት አስተያየት፤ በተያዘዉ 2017 የትምህርት ዘመን የብሔራዊ ፈተና ለመዉሰድ ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸዉን ገልጸዋል፡፡
ተማሪዎቹ በትምህርት ቤቱ ደንብና መመሪያ መሰረት በስነ-ምግባር ታንፀዉ ትምህርታቸዉን በመከታታል የተሻለ ዉጤት ለማምጣት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በየትምህርት ቤቶቻቸዉ የመማሪያ መጽሀፍት እጥረት፣ ጥራት ያለዉ ትምህርት ያለመሰጠት እንዲሁም በአንድ አንድ የትምህርት አይነቶች የመምህራን እጥረት እንዳለም ተማሪዎቹ ገልፀዋል።
በተለይ በቀቤና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሒሳብ እና የኢኮኖሚክስ ትምህርት በአግባቡ እየተማሩ እንዳልሆነ ተማሪዎቹ በመግለፅ ችግሩ እንዲቀረፍ ጠይቀዋል።
የቀቤና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ተወካይ መምህር ሀምዲሳ ሙዘሚል እና የሀሰን ዑንጃሞ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር መሀመድ ሁሴን በሰጡት አስተያየት፤ ተማሪዎች ትምህርታቸዉን በአግባቡ እንዲከታተሉ በማድረግ ጥሩ ዉጤት እንዲያመጡ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ከመምህራን እና ከመማሪያ መጽሀፍት እጥረት ጋር ተማሪዎች ላነሱት ችግር ለመቅረፍ ከልዩ ወረዳዉ ትምህርት ፅ/ቤት ጋር እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የቀቤና ልዩ ወረዳ ትምህርት ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ አህመድ ሀሰን እንዳሉት፤ በልዩ ወረዳዉ ባለፉት ዓመታት ያጋጠመውን የትምህርት ጥራት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋራ በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል።
በትምህርት ዘመኑ ተማሪዎች ጥራት ያለዉ ትምህርት ማግኘት እንዲችሉ ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ምቹ እንዲሆኑ መደረጉን ሀላፊዉ ገልፀዋል።
በተያዘዉ የትምህርት ዘመን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸዉ እንዳይፈናቀሉ ህብረተሰቡን በማስተባበር ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ ከ2 ሺህ 600 በላይ ተማሪዎችን የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቶች አቅም ባላቸዉ አመራር መመራት እንዳለባቸዉ የክልሉ መንግስት ባስቀመጠዉ አቅጣጫ በልዩ ወረዳዉ የትምህርት አመራር ሪፎርም እየተደረገ መሆኑን የገለፁት አቶ አህመድ ይህም በዘርፉ የተሻለ ዉጤት ለማስመዝገብ ጉልህ ሚና እንዳለዉ አመላክተዋል።
ተማሪዎች የመማሪያ መጽሀፍት እንዲያገኙ ፅ/ቤቱ እየሰራ ይገኛል ያሉት ሀላፊዉ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በቂ መኖሩንና ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ ተደራሽ ይደረጋል ብለዋል።
ለመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመማሪያ መጽሀፍት በልዩ ወረዳዉ በህብረተሰብ ተሳትፎ በተገኘ 4 ሚሊዮን ብር ግዢ መፈፀሙንና አሁን ለትምህርት ቤቶች ተደራሽ ይደረጋል ብለዋል።
በአገር አቀፍ ፈተናዎች በተለይ በስድስተኛ እና በስምንተኛ ክፍል ከባለፈዉ አመት የተሻለ ዉጤት መመዘገቡንና ይህንን ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል።
በ12ኛ ክፍል የማጠናቀቂያ ፈተና የገጠሙ ችግሮችን በጥናት ለመፍታት ፅ/ቤቱ በትኩረት ይሰራል ያሉት ሀላፊዉ ተማሪዎች ልዩ ድጋፍ እንዲያገኙ ከወልቂጤ ዩኒቨርስቲ እና ከሆሳዕና መምህራን ኮሌጅ ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የተማሪዎች ዉጤት ለማሻሻል በሚደረገዉ ጥረት ሁሉም የትምህርት ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ እንደሚገባም ሀላፊዉ አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፡ ሪያድ ሙህዲን – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
“ዞናዊ አንድነት ለጋራ ህልሞቻችን ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ የዞኑ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላትን ጨምሮ የዞኑ ተወላጅ የክልል አመራሮች የዞን ጠቅላላ አመራር እና የየወረዳ የፊት አመራሮች የምክክር መድረክ በደቡብ ኦሞ ዞን ዲመካ ከተማ እየተካሄደ ነዉ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት የበጀት ቀመር አሰራርና የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሔደ ይገኛል
በዳውሮ ዞን ማረቃ ወረዳ የዋካ ከተማ በአዲሱ መዋቅር የከተማ አስተዳደር በማግኘቷ መደሰታቸውን ነዋሪዎቿ ገለፁ