ሀዋሳ፡ ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የወባ በሽታ ስርጭት ከህዳር መግቢያ እስከ ቀጣዩ ታህሳስ ወር መጨረሻ ድረስ ሊጨምር ስለሚችል ህብረተሰቡን የማስገንዘብ የመገናኛ ብዙሃን ሚና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስገነዘበ።
ቢሮው በወባ ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር ዙሪያ በቡታጅራ ከተማ ለመገናኛ ብዙሃን ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ አካሂዷል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ በውይይት መድረኩ ላይ እንደተናገሩት፤ ወረርሽኙ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ በክልሉ የሚገኙ የመገናኛ ብዙሃን በመከላልና በመቆጣጠር ስራ ጉልህ ድርሻ አበርክተዋል።
የክልሉ ጤና መዋቅርም በክልሉ ለወባ በሽታ ይበልጥ ተጋለጭ የሆኑ 120 ቀበሌያትን በመለየት ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ስራ መስራቱን ጠቁመዋል።
የወባ ትንኝ መራቢያ ሊሆን የሚችል ዉሃን የማፈሰስና የማዳፈን ተግባር በየቀበሌያቱ መፈጸሙን የገለጹት አቶ ሳሙኤል ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ በሆኑ አካባቢዎች የቤት ለቤት ኬሚካል ርጭት መደረጉንም ተናግረዋል።
የወባ በሽታ ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢመጣም በተሠራዉ የተቀናጀ የመከላከል ስራ ከተቀመጠዉ ሰጋት አንጻር የከፋ ጉዳት አለመድረሱን ኃላፊዉ ተናግረዋል።
ከህዳር መግቢያ አስከ ታህሣሥ መጨረሻ ድረስ የበሽታዉ ስርጭት ሊጨምር ስለሚችል ህብረተሰቡን የማስገንዘብ የመገናኛ ብዙሃን ሚና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አቶ ሳሙኤል አስገንዝበዋል።
የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት መድረኩ የወባ በሽታ ስርጭት መከላከል ስራውን አጠናክረን እንድንሰራ ግንዛቤ የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በአጎበር አጠቃቀምና ስርጭት እና በመንግስት ጤና ተቋማት ላይ የመድሀኒት አቅርቦት እጥረት እንዳለ ለሚዲያ ተቋማት በህብረተሰቡ አስተያየት እየቀረበ ስለሆነ ክትትሉ መጠናከር አለበት ብለዋል።
በዉይይት መድረኩ የክልል፣ የዞንና ልዩ ወረዳ የኮሙኒኬሽን እና የሚዲያ ኃላፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ዘጋቢ: ደመቀ ጀንበሬ – ወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
“ዞናዊ አንድነት ለጋራ ህልሞቻችን ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ የዞኑ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላትን ጨምሮ የዞኑ ተወላጅ የክልል አመራሮች የዞን ጠቅላላ አመራር እና የየወረዳ የፊት አመራሮች የምክክር መድረክ በደቡብ ኦሞ ዞን ዲመካ ከተማ እየተካሄደ ነዉ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት የበጀት ቀመር አሰራርና የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሔደ ይገኛል
በዳውሮ ዞን ማረቃ ወረዳ የዋካ ከተማ በአዲሱ መዋቅር የከተማ አስተዳደር በማግኘቷ መደሰታቸውን ነዋሪዎቿ ገለፁ