በክልሉ ያለው የጤና ኤክስቴንሽን ስርዓት ውጤታማ እንዲሆንና ፖሊሲው በተገቢው መልኩ እንዲተገበር ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ገለፀ

የክልሉ ጤና ቢሮው የበሽታ መከላከልና ጤና ማጎልበት ዳይሬክቶሬት የ2016 በጀት አመት ዕቅድ አፈጻጸምና የ2017 የመጀመሪያ ሩብ አመት አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊና የፕሮግራሞች ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሀይሌ ዘውዴ እንደተናገሩት፤ የማህበረሰቡን ጤና ለመጠበቅና በሽታዎችን አስቀድሞ በመከላከል ረገድ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም አይነተኛ ሚና አለው።

በክልሉ ያለውን የጤና ኤክስቴንሽን ስርዓት ውጤታማ እንዲሆንና ፖሊሲው በተገቢው መልኩ እንዲተገበር ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በክልሉ ባለፈው በጀት አመት የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ውጤታማ እንዲሆን በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ አመራሮችንና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን በማሳተፍ በንቅናቄ ሲሰራ እንደነበር ተናግረዋል።

በተለይ በ2016 በጀት አመት በክልሉ ከሚገኙ 844 ቀበሌያት የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብሩን በተገቢው በመፈፀም 390 የሚሆኑ ቀበሌያት ሞዴል ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

ሌላው በክልሉ በሚገኙ የጤና ተቋማት የሚታዩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለማሻሻል በትኩረት ሲሰራ እንደነበር ተናግረዋል።

በክልሉ ተላላፊ ያልሆኑ እንደ ስኳርና ደም ግፊትን የመሳሰሉ በሽታዎች መጠንና ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መምጣታቸውን የተናገሩት አቶ ሀይሌ፤ እነዚህን በሽታዎች ለመከላከል የማህበረሰቡን የአኗኗርና አመጋገብ ባህል እንዲቀየር የግንዛቤ ስራ መስራት ይገባል ብለዋል።

በተለይ በክልሉ በአሁኑ ወቅት ለማህበረሰቡ አንገብጋቢ ከሆኑ የጤና ችግሮች መካከል የወባ ወረርሽኝ አንዱና ዋነኛው መሆኑን ያነሱት አቶ ሀይሌ፤ ይህንን ለመከላከል የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ይጠይቃል ነው ያሉት።

ቢሮው ወባን ለመከላከል የሚያስችሉ ስራዎችን ከመስራት ባለፈ በጤና ተቋማት የሚታዩትን የመድኃኒትና የህክምና ቁሳቁሶች ችግር ለመፍታት ከፌዴራል ጤና ሚኒስቴርና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ የቢሮው የበሽታ መከላከልና ጤና ማጎልበት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር እንዳለ ሳህሌ፤ በአጠቃላይ የተከናወኑ ስራዎችንና ያጋጠሙ ችግሮች በዝርዝር ሪፖርት አቅርበው ውይይት ተደርጓል።

በመድረኩ የተሳተፉ አካላት በሰጡት ሀሳብና አስተያየትም በክልሉ ባለፈው አመት የተሰሩ የጤና ኤክስቴንሽንና የበሽታ መከላከል ስራዎች የተሻሉ እንደነበር ጠቁመዋል።

ባለፈው አመት በየአካባቢው ከወባ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ጉዳት በህብረተሰቡ ላይ ሲያደርስ እንደነበር ተሳታፊዎች ተናግረው በተያዘው አመት ይህንን ለመከላከል የሚያስችል የተጠናከረ ስራ ይጠበቃል ብለዋል።

ዘጋቢ፡ ጦያር ይማም – ከሚዛን ጣቢያችን