የጋሞ ዞን ሥራ ዕድል ፈጠራ ምክር ቤት የሥራ ዕድል ፈጠራ ተግዳሮቶችና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የንቅናቄ መድረክ በአርባምንጭ ከተማ አካሄደ

በዞኑ ያሉ ፀጋዎችንና አቅሞችን በመጠቀም ቀጣይነት ያለው የሥራ ዕድል ለመፍጠር የአደረጃጀትና ቅንጅታዊ ድጋፍና ክትትል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አጽንኦት ተሰጥቷል።

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የሥራ ዕድል ፈጠራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ አባይነ አበራ በፍትሃዊነት ሥራ አጥ ወጣቶች ልየታ፣ የመስሪያና የማምረቻ ቦታ ማዘጋጀትና ብድር አመላለስ ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶችን በመፍታት በዞናችን ያሉ ፀጋዎችን በመጠቀም ቀጣይነት ያለው የሥራ ዕድል በመፍጠር የብልጽግና ጉዞአችንን ማፋጠን ይገባል ብለዋል።

የጋሞ ዞን የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አበራ፤ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ በማኑፋክቸሪንግ፣ በገጠርና በከተማ ጥቃቅን፣ በአነስተኛና በመካከለኛ 4 ሺህ 689 ማህበራት ተደራጅተው ሥራ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት 48 ሺህ 679 ሥራ አጥ ወጣቶችን ለይቶ ወደ ስራ ለማስገባት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ 20 ሺህ 336ቱ ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዞኑ ባሉ ሁሉም መዋቅሮች ከሚታዩ ተግዳሮቶች መካከል የአሠራርና አደረጃጀት መመሪያ ተከትሎ የቁጥጥርና ድጋፍ ቅንጅታዊ ሥራ መጓደል፣ የመሬትና የሼድ አቅርቦት፣ ብድር አቅርቦትና አመላለስ ችግሮች በውይይቱ ነጥረው ወጥተዋል።

ችግሩን ለመፍታት በበጀት ዓመቱ ስራ አጥ ወጣቱን በገጠርና በከተማ በከብት እርባታ፣ በዶሮ፣ በማርና በዓሳ ልማት ላይ ትኩረት በማድረግ እንቅስቃሴ መደረጉ ተመላክቷል።

ዘጋቢ፡ ማስረሻ ዘውዴ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን