የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በዞኑ ለሚገኙ የመሬት መንሸራተት አደጋ ተጎጂዎች ከ33 ሚሊየን ብር በላይ ፕሮጀክት ቀርጾ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በዞኑ ለሚገኙ የመሬት መንሸራተት አደጋ ተጎጂዎች ከ33 ሚሊየን ብር በላይ ፕሮጀክት ቀርጾ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ተጎጂዎች ከ33 ሚሊየን ብር በላይ ፕሮጀክት ቀርጾ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።

ማህበሩ ለተጎጂ ቤተሰቦች 7 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉም ተመላክቷል።

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በጎፋ ዞን በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ማቋቋሚያ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አሰማ ግርማ እንደገለጹት፤ ማህበሩ ከጀርመን ቀይ መስቀል ማህበር ጋር በመተባበር በጎፋ ዞን ጉዳት ለደረሰባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ቀጥሏል።

ማህበሩ ተጎጂዎችን ለማቋቋም ከ33 ሚሊየን ብር በላይ ፕሮጀክት ቀርጾ ድጋፍ እያደረገ ሲሆን የቁሳቁስ፣ የገንዘብ እና የውሃ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አደጋው ከተከሰተበት ዕለት ጀምሮ ለተጎጂዎች አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ በማድረግ ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ መሆኑን በተግባር ሲያሳይ መቆየቱን አንስተዋል።

ተጎጂዎችን ለማቋቋም ከክልሉና ከዞኑ መንግስት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የጎፋ ዞን ቀይ መስቀል ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ አቶ ኢያሱ ጣሰው በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አደጋው ከተከሰተበት ዕለት ጀምሮ በርካታ ሰብዓዊና ቁሳዊ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።

በአደጋው ለተፈናቀሉ 627 አባዎራዎች እና እማወራዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ሰባት ዓይነት የተለያዩ የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶችና የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ መደረጉን ጠቁመዋል።

ማህበሩ ከጀርመን ቀይ መስቀል ማህበርና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ሁለት የውሃ ፕሮጀክቶችን ግንባታ ለማከናወን ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን አስረድተዋል።

ማህበሩ ተጎጂዎች በሚደረግላቸው ምግብ ነክ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ብቻ ፍላጎታቸውን ማሟላት ስለማይችሉ ለእያንዳንዱ አባወራና እማወራ 6ሺህ 970 ብር በሁለት ዙር ክፍያ ለመፈጸም ዝግጅት መጠናቀቁን የማህበሩ የክፍያ ኦፊሰር የሆኑት አቶ አለምሰገድ መኮንን ገልጸዋል።

ካነጋገርናቸው ተረጂዎች መካከል አቶ መምህሩ መኩሪያ፣ ወ/ሮ አልማዝ ላዴ እና አቶ ግርማ ቶዜ ማህበሩ ላደረገው የቁሳቁስ ድጋው ምስጋና አቅርበዋል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን