በ2017 ዓ.ም 1ኛ ሩብ ዓመት በክልሉ በዋና ዋና ዘርፎች ተስፋ ሰጪ ለውጦች መመዝገባቸውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ

በ2017 ዓ.ም 1ኛ ሩብ ዓመት በክልሉ በዋና ዋና ዘርፎች ተስፋ ሰጪ ለውጦች መመዝገባቸውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ

ቢሮው በበጀት ዓመቱ 1ኛ ሩብ ዓመት በክልሉ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት ዙሪያ መገለጫ ሰጥቷል፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ በረከት እዮብ፤ በክልሉ ባለፉት ሶስት ወራት በዋና ዋና ዘርፎች ላይ ተስፋ ሰጪ ለውጦች መመዝገባቸውን አስረድተዋል፡፡

በክልሉ በተያዘዉ መኸር አዝመራ 345 ሺህ 664 ሄክታር መሬት በማልማት 7 ሚሊየን 5 መቶ 86 ሺህ 3 መቶ 82 ኩንታል ምርት ለማምረት በትኩረት እየተሰራ ነዉም ብለዋል፡፡

እንደሀገር በተከናወነው በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በክልሉ በሩብ ዓመቱ 145 ሚሊዮን 628 ሺህ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያሏቸው ችግኞች መተከላቸውን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ 11 ሺህ 7 መቶ 26 ቶን ቡና እና 3 ሺህ 1 መቶ 95 ቶን ቅመማ ቅመም በ1ኛ ሩብ ዓመት ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል ብለዋል፡፡

በ2016/17 የምርት ዘመን 79 ሺህ 394 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ በብድር መሰራጨቱን የተናገሩት ወ/ሮ በረከት ከዚህም 122 ሚሊዮን 110 ሺህ 242 ብር ማስመለስ መቻሉንም በመግለጫቸው አስረድተዋል፡፡

የክልሉን ኢንቨስትመንት ከማጠናከር አኳያ በግብርና ለ11፣ በኢንዱስትሪ 3 እና በአገልግሎት 6 ፕሮጀክቶች አዲስ ፍቃድ መሰጠቱን ጠቁመው፥ ከእነዚህ ኢንቨስትመንት ዘርፎች 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ካፒታል ተመዝግቧል ብለዋል፡፡

እንደ ክልል ህገ-ወጥነትንና ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ቁጥጥር ለማድረግ በተደረገው ጥረት 11 ሺህ 471 ሊትር ቤንዚን እና 1 ሺህ 960 ሊትር ናፍጣ በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጸው በህገ ወጥ ተግባር የተሰማሩ  አካላት ላይ እርምጃ ተወሰዷል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ 1ኛ ሩብ ዓመት 2 ቢሊዮን 316 ሚሊዮን 366 ሺህ 624 ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 1 ቢሊዮን 833 ሚሊዮን 262 ሺህ ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉም በመግለጫው ተካቷል።

አፈጻጸሙ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 5 መቶ 88 ሚሊዮን 3መቶ 63 ሺህ 7መቶ 67ብር ብልጫ እንዳለው ተነሰቷል፡፡

በክልሉ አርብቶና ቆላማ አካባቢ ያሉ ዜጎች የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ በተደረገዉ ጥረት 1 መቶ 79 ተማሪዎች በ2 በአዳሪ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እየተደረገ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የህብረተሰቡን የንጹህ መጠጥ ውሃ ፍላጎት ለማሟላት በ1ኛ ሩብ ዓመት አዳዲስ የጥናትና ዲዛይን ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን በመግለጫቸው ያነሱት ምክትል ኃላፊዋ፤ በ2ኛ ሩብ ዓመት የጨረታ ሂደቱን ተከትሎ ወደ ግንባታ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

29 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ መላክ መቻሉንም በመግለጫቸው ጠቁመዋል።

በመስኖ ልማት ዘርፍ በሩብ ዓመቱ 67 የመስኖ አውታሮች በሙሉ አቅም 8ቱ በከፊል በማልማት የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነቱን እንዲያረጋግጥ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በክልሉ በተለያዩ ከተሞች ሰነድ አልባ ይዞታዎች ሰነድ እንዲያገኙ እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን  ተናግረዋል።

በጤናው ዘርፍ የወባ ስርጭት የመከላከል ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በክልሉ መንግስት አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል።

በክልሉ ቦንጋ፣ ዋቻ ከተማና ሚዛን አማን ከተማ የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ወደ ሌሎች አካባቢዎች መስፋት እንዳለበት በክልሉ መንግስት አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ብዙአየሁ ጫካ – ቦንጋ ጣቢያችን