የሃይማኖት ተቋማት ከሃይማኖታዊ አስተምሮ ባለፈ ለቋንቋ ዕድገት የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የሀድያ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ገለጸ
በኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር የተዘጋጀ የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ በድምጽ ማድመጫ መሳሪያ ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።
አቶ ተካበ ንዋይ በኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር የሰው ኃይል አስተዳደርና እምነት ከመስማት ይመጣል ፕሮጀክት ብሄራዊ አስተባባሪ ናቸው።
ማህበሩ ከዚህ ቀደም መጽሐፍ ቅዱስ በሀዲይሳ ቋንቋ ተተርጉሞ እንዲዘጋጅ ያደረገ ሲሆን በሌሎች ልማታዊ ተግባራትም በመሳተፍ ሃገራዊ ድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በአሁኑ ጊዜም አሜሪካን ሀገር ከሚገኘው “እምነት ከመስማት ይመጣል” ከተሰኘ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተዘጋጀ የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ በድምጽ የተቀረጸ መሳሪያ ለማስመረቅ መቻሉን ገልጸዋል።
የድምጽ መሳሪያው በስራ መብዛት፣ ባለመማር፣ ባለማየትና በሌሎችም ምክንያቶች ማንበብ የማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በድምጽ በመስማት እንዲረዱ የሚያግዝ ስለመሆኑም አንስተዋል።
የድምፅ መሣሪያው በጉራጊኛ፣ በሲዳምኛ፣ በወላይትኛና በሀድይሳ ቋንቋዎች የሚያገለግል ስለመሆኑም አቶ ተካበ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር ከዛሬ አርባ ዓመታት በፊት ጀምሮ በቋንቋዎች ዕድገት አስተዋጽኦ እያደረገ የቆየ መሆኑንና በአሁኑ ጊዜም ሰዎች የእምነታቸው መሠረት የሆነውን ቃሉን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በድምጽ እንዲረዱ ከማድረግም ባለፈ ለቋንቋ ዕድገት ያደረገው አስተዋጽኦ የሚበረታታ ነው ያሉት ደግሞ በማህበሩ የሀድያ ዞን የቋንቋዎች አስተባባሪ አቶ አብርሃም ለዕላጎ ናቸው።
በመርሃ ግብሩ የተገኙት የሃድያ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ተወካይ አቶ ዘለቀ አደም እንደገለጹት የድምፅ መሳሪያ በአፍ መፍቻ ቋንቋዎች መዘጋጀቱ ከሃይማኖታዊ አስተምሮ ባለፈ ለቋንቋ ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የጎላ ነው።
የድምጽ ማድመጫ መሳሪያው በተያዘለት ጊዜ ወደ ህዝቡ ተደራሽ ሆኖ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጥ በትኩረት እንዲሰራም ጠይቀዋል።
በመርሃ ግብሩ የተለያዩ ቤተ እምነት መሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ያነጋገርናቸው መሪዎችና ሌሎች ተሳታፊዎች በበኩላቸው በተለያዩ ምክንያቶች ቃሉን ማንበብ ለማይችሉ ምዕመናን በቀላሉ የሚሰሙበት ትልቅ ጠቀሜታ ያለው የድምፅ ማድመጫ መሳሪያ ነው ብለዋል።
የእምነት ተቋማት ትውልድን የማነፅ ኃላፊነት ያላቸው እንደመሆናቸው በተለያዩ ምክንያቶች ማንበብ ለማይችሉ ሰዎች በመሣሪያው በመታገዝ እንዲሰሙ በማድረግ መሪዎች የድርሻቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡ ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የነዳጅ እና ቤንዚን ምርቶች ስርጭት ላይ የሚስተዋለውን ኢፍትሃዊነት ለመቅረፍ ጠንከር ያለ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያስፈልግ የወላይታ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መመሪያ አስታወቀ
ሰላምና ፀጥታ በዘላቂነት ለማረጋገጥ ማህበረሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባ ተገለፀ
ወሳኝ ኩነት ምዝገባ የልማት፣ የዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ግንባታ ሂደት ለማፋጠን ድርሻው ከፍተኛ እንደሆነ ተገለፀ