በአሁን ወቅት አጠቃላይ ካፒታሉን ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በማድረስ እየሠራ እንደሚገኝ የጂንካ መምህራን የገንዘብ ቁጠባና ብድር መሠረታዊ ህብረት ሥራ ኃላፊነቱ የተወሰነ ማህበር አስታወቀ
የአባል መምህራንን ኢኮኖሚ ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስና በአካባቢው ከመንግስት ጎን በመቆም በልማታዊ ሥራዎች ተሳታፊና ተጠቃሚ ለመሆን ታስቦ የተቋቋመው ማህበሩ 20ኛ ዓመት ጉበኤውን አካሂዷል።
ከዛሬ 20 ዓመት በፊት በ1996 ዓ.ም በ72 አባላት የተቋቋመው የጂንካ መምህራን የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር ዛሬ ላይ የአባላት ቁጥሩ ከ293 በላይ አድርሶ በተለያዩ ዘርፎች ሐብት የማፍራት ተግባር እያከናወነ እንደሚገኝ የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ ዘላለም ጌታቸው አስረድተዋል።
ማህበሩ ለአባላት የትርፍ ክፍፍል እያደረገና ተጨማሪ ዕጣ በመሸጥ የማህበሩ አባላት ተሳትፎ እንዲያድግ ብሎም አዳዲስ አባላትን በማፍራት እየሠራ እንደሚገኝ ሰብሳቢው ገልፀዋል።
ማህበሩ በይፋ ተመስርቶ ወደ ሥራ ሲገባ በየወሩ አምስት ሺህ ብር ከአባላት መዋጮ በማድረግ ያስቀጥ እንደነበር የሚያስታውሱት ሰብሳቢው፤ ዛሬ ላይ ይህንን አሃዝ ወደ ከ6 መቶ ሺህ ብር በላይ በወር ማድረስ ተችሏል ብለዋል።
በከተማው ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለተለያየ አገልግሎት የሚውል ህንፃ ለማስገንባት ግዢ ስለመፈፀሙም ተገልጿል።
ከዚህ በፊት የከተማ አስተዳደሩ ቦታ እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ እንደነበርና በአሁን ወቅት ጥሩ ምላሽ መኖሩን የጠቀሱት አቶ ዘላለም ይህ ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባር እንዲቀየር ጠይቀዋል።
በአሁን ወቅት ማህበሩ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል እንዳለውም ተገልጿል።
ጥቂት አባላት በወቅቱ ብድር ያለመመለስ፣ የቢሮ አደረጃጀት እና መሰል ችግሮች ማህበሩ በሚፈልገው ልክ እንዳይንቀሳቀስ ማነቆ ስለመሆናቸው በቀረበው ሪፖርት ተካቷል።
በመድረኩ የተገኙት የኣሪ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ጉራልቅ ይዥማልቅ፤ በጋራ ተባብሮ ሕብረት ፈጥሮ ሐብት ማፍራት ዙሪያ ያለውን ችግር በመቅረፍ በአቋም ቁጠባ በማድረግ የተሻለ ደረጃ ላይ ያለው የመምህራን ብድርና ቁጠባ ተቋም ሥራው የሚበረታታ ነው ብለዋል።
ለ20 ዓመታት በዘርፉ ያሉ ችግሮች ቢኖሩም በመቋቋም ዛሬ ላይ ከክልሉ ዕውቅ የሆነ ማህበር ሆኖ የበቃው፤ በቀጣይም አድማሱን ይበልጥ በማስፋት በአካባቢው የልማት ክፍተቶችን በመሸፈን ለራሱም ለአካባቢውም ጥቅም ተግቶ እንዲሠራ ጥሪ ያቀረቡት አቶ ጉራልቅ ለማህበሩ በመንግስት በኩል የሚፈለገውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል።
የኣሪ ዞን ህብረት ሥራ ልማት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ምስጋናው ማናዬና የዞኑ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ሀላፊ አቶ ፍቅረስላሴ ጀማል በጋራ እንደገለፁት፤ ለማህበሩ የተለያዩ ድጋፎች እንደሚደረጉ ገልፀዋል።
በጉባኤው የክንውንና የኦዲት ሪፖርት እንዲሁም ቀጣይ የሥራ አቅጣጫን የሚያመላክት ዕቅድ ቀርቦ በአባላቱ ገንቢ አስተያየት ተሰጥቶበታል።
ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
በማህበረሰቡ ውስጥ የተለመዱና የተዛቡ የስርዓተ ጾታ አመለካከቶችን ለመቅረፍ ተከታታይ የአቅም ግንባታ ስራዎችን መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ
የነዳጅ እና ቤንዚን ምርቶች ስርጭት ላይ የሚስተዋለውን ኢፍትሃዊነት ለመቅረፍ ጠንከር ያለ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያስፈልግ የወላይታ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መመሪያ አስታወቀ
ሰላምና ፀጥታ በዘላቂነት ለማረጋገጥ ማህበረሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባ ተገለፀ