ሀዋሳ፡ ጥቅምት 23/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ሬድዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ጂንካ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት በሠላም ግንባታ ላይ በአካባቢዉ ቋንቋዎች ተደራሽ ለማድረግ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ዉማን ኢምፓወርመንት ከተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በደቡብ ኦሞ ዞን በሐመር ወረዳ በሠላም እሴት ግንባታ እና በሴቶች እኩልነት ላይ ያተኮረ ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራርሟል።
የዉማን ኢምፓወርሜንት የመስክ ጽ/ቤት አስተባባሪ አቶ ታምራት መሳቶ እንደገለፁት በዞኑ ሐመር ወረዳ የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታትና ማህበረሰቡ ስለሠላም አስፈላጊነት ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ ለ3 ዓመት ያህል በራዲዮ ኘሮግራም ተደራሽ ለመሆን እንደሚሠራ ገልጸው የመግባቢያ ስምምነቱም ይህንን ያለመ እንደሆነ ገልፀዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፍ አቶ ጎላ ጉዳቦ በበኩላቸው ከአጋር ድርጅቶች ጋር በተደረገዉ ዉይይት በርካታ ግብአቶች እንዳገኙና በቀጣይ የሠላም ግንባታን ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙርያ ከደቡብ ራዲዮ ጂንካ ቅርንጫፍ ጋር በቅንጅት እንደሚስሩ ተናግረዋል።
የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ጂንካ ቅርንጫፍ ዋና ሥራ አስክያጅ አቶ ሙሉዋስ አቲሳ እንደገለፁት ተቋሙ ከስምንት የተለያዩ አጋር አካላት ጋር በልዩ ሁኔታ በተለያዩ የአካባቢ ቋንቋዎች የራዲዮ ኘሮግራም አዘጋጅቶ ከመደበኛ ዝግጅቱ በተጨማሪ እየሠራ ነው ብለዋል።
ግብረሰናይ ድርጅቶችም በድርጅቱ የማስታወቂያና ፕሮግራም መመሪያ መሰረት አስፈላጊዉን የሚፈፅሙ ሲሆን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ከቁሳቁስ አንፃር ያለዉን ክፍተት ለመሙላትም የበኩላቸዉን አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆኑን አዉስተዋል።
በቀጣይም ቅንጅታዊ አሰራርን ይበልጥ በማጠናከር ለሠላም ግንባታ የበኩሉን በጎ ሚና እንደሚጫወትም ዋና ሥራ አስክያጁ በመግባቢያ ሰምምነቱ ወቅት ገልፀዋል።
ከተሳታፊ ባለድርሻ አካላትም የተለያዩ ጥያቄና አስተያየቶች ተነስተው በመድረኩ መሪዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰቶባቸዋል።
በመግባቢያ ስምምነቱ ላይ የደቡብ ኦሞ ዞን ሠላምና ፀጥታ መምሪያ፣ የኮሚኒኬሽን ባለሙያዎች፣ የደቡብ ራዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ጂንካ ቅርንጫፍ የራዲዮ ኬዝ አስተባባሪና አርታኢዎች የቋንቋ ተርጓሚና አዘጋጆች፣ አርታኢያንና ሌሎች የሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት ተገኝተውበታል።
ዘጋቢ: ሁሰን አለሙ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
በማህበረሰቡ ውስጥ የተለመዱና የተዛቡ የስርዓተ ጾታ አመለካከቶችን ለመቅረፍ ተከታታይ የአቅም ግንባታ ስራዎችን መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ
የነዳጅ እና ቤንዚን ምርቶች ስርጭት ላይ የሚስተዋለውን ኢፍትሃዊነት ለመቅረፍ ጠንከር ያለ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያስፈልግ የወላይታ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መመሪያ አስታወቀ
ሰላምና ፀጥታ በዘላቂነት ለማረጋገጥ ማህበረሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባ ተገለፀ