ሀዋሳ፡ ጥቅምት 23/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዕውቀትና በመልካም ስነ ምግባር የታነፁ ዜጎችን መፍጠር የሚችሉ ብቁ መምህራንን የማፍራት ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ የሆሳዕና ትምህርት ኮሌጅ አስታወቀ።
ኮሌጁ በ2017 የትምህርት ዘመን በዲፕሎማና በዲግሪ ፕሮግራም ከ700 በላይ ነባር ተማሪዎችን ተቀብሎ የመማር ማስተማር ስራዉን የጀመረ ሲሆን፥ ከ700 በላይ አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል።
የትምህርት ኮሌጆች በዕውቀትና በመልካም ስነ ምግባር የታነፁ ዜጎችን መፍጠር የሚችሉ ብቁ መምህራንን በማፍራት ረገድ ሚናቸው የጎላ ለመሆኑ ተመላክቷል።
የሆሣዕና ትምህርት ኮሌጅ በዘርፉ ውጤታማ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ የኮሌጁ የአካዳሚክና ምርምር ምክትል ዲን አቶ ተካ ሞጬ ገልጸዋል።
በ2017 የትምህርት ዘመን በዲፕሎማና በዲግሪ ፕሮግራም ከ700 በላይ ነባር ተማሪዎች ትምህርታቸውን የጀመሩ ሲሆን ከነዚህም ዉስጥ 360 የዲግሪ ፕሮግራም ተማሪዎች ስለመሆናቸው አቶ ተካ ጠቁመዋል።
በዲኘሎማ እና በዲግሪ ፕሮግራም 760 አዲስ ተማሪዎችን በመቀበል በተመረጡ የትምህርት መስኮች ለማስተማር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ጊዜ ትኩረት የተሰጠውን የቅድመ መደበኛ ደረጃ ትምህርት በተመለከተም ከንድፈ ሃሳብ ይልቅ ለተግባር ትምህርት የተደራጀ ማዕከል በማዘጋጀትና በዘርፉ በቂ ልምድ ባላቸው መምህራን በማስተማር ብቁ መምህራንን ለማፍራት እየተሰራ ይገኛል ያሉት የኮሌጁ ዲን በዚህ ዓመትም በሰርትፊኬት ደረጃ ለመቀበል ዝግጅት ስለመደረጉ አመላክተዋል።
ለዚህም በኮሌጅ ውስጥ አገልግሎት እየሰጠ ያለው የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ሰልጣኝ መምህራን ስልጠናውን በተግባር የሚያሳዩበት ማዕከል ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
አንዳንድ የኮሌጁ መምህራን በበኩላቸው በቂ የሙያ ብቃት ተክነው ጥራት ባለው ትምህርት ትውልድን መቅረጽ የሚችሉ መምህራንን ለማፍራት እየተጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በኮሌጁ ለትምህርት ስራ ውጤታማነት አጋዥ የሆኑ የተደራጁ ማዕከላትን በመጠቀም በተግባር የተደገፈ ትምህርት እየሰጡ ስለመሆናቸውም አስረድተዋል።
ከኮሌጁ ተማሪዎች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡን አስተያየት በኮሌጁ እየተሰጠ ያለው ትምህርት በሙያው የበቁ እንዲሆኑ የሚያስችል እንደሆነ ገልጸዋል።
ከክፍል ውስጥ ትምህርት ባለፈ ቤተመጻህፍት፣ ቤተ ሙከራ፣ አይ ሲ ቲ እና መሰል የተደራጁ ማዕከላትን በመጠቀም ጠንካራ የሙያ ባለቤት ለመሆን የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ ስለመሆናቸው ተማሪዎቹ አክለዋል።
ዘጋቢ፡ ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
በማህበረሰቡ ውስጥ የተለመዱና የተዛቡ የስርዓተ ጾታ አመለካከቶችን ለመቅረፍ ተከታታይ የአቅም ግንባታ ስራዎችን መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ
የነዳጅ እና ቤንዚን ምርቶች ስርጭት ላይ የሚስተዋለውን ኢፍትሃዊነት ለመቅረፍ ጠንከር ያለ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያስፈልግ የወላይታ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መመሪያ አስታወቀ
ሰላምና ፀጥታ በዘላቂነት ለማረጋገጥ ማህበረሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባ ተገለፀ