በስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ዘርፍ የሚስተዋሉ የአሰራር ውስንነቶችን በመፍታት የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ጥቅምት 16/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው በተገኙበት የተካሔደው ጉባኤ፥ በዘርፉ የሚስተዋሉ የአሰራር ውስንነቶችን በመፍታት የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሊሰራ እንደሚገባ የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ አስታወቋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው በሰጡት የስራ መመሪያ፥ ከስራ አጥነትና ስራ ዕድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ መረዳት አንደሚገባ ጠቁመው፥ ስራ የምንፈጥርባቸውን መስኮች በሚገባ በመፈተሽና በመለየት ለሚደራጁ ስራ አጥ ዜጎች ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በጊዜያዊ የስራ ዕድልና በቋሚ የስራ ዕድል መካከል ያለውን ልዩነት ማመጣጠን እንደሚገባ ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የሚሰጡ የድጋፍ ፓኬጆችን በሚገባ ተግባራዊ በማድረግ በተለይ ድጋፎችን በመለየት፣ በማደራጀትና በማሰልጠን የስራ ስምሪት መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተቀመጠላቸው የጊዜ ቆይታ ውስጥ የበቁ ማህበራትንና ኢንተርፕራይዞችን ወደሚቀጥለው ደረጃ በማሸጋገር የመስሪያ ቦታና የተያዙ ሼዶችን በማስለቀቅ፥ አዳዲስ የሚደራጁ ማህበራትን የሼዶች ተጠቃሚ በማድረግ ወደ ስራ እንዲገቡ ማገዝ ያስፈልጋል ብለዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መሀመድ ኑርዬ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፥ የስራ ፈጠራ ማዕከል ኢንተርፕራይዞች መሆናቸውን ጠቁመው፥ በአዳዲስ ሃሳቦች ላይ ኢንቨስት ከማድረግ ባለፈ የማህበረሰባችንን ፍላጎት የሚያሟሉ ምርቶችና አገልግሎቶችን የሚያቀርቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ክልሉ በአዲስ መልኩ ከተደራጀ በኋላ በዘርፉ ለዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር መጠነ ሰፊ ርብርብ ማደረጉን አመላክተው፥ የስራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ ስራ ፈላጊ ዜጎችን በመለየት፣ በማደራጀት፣ አዋጭነታቸው በተረጋገጡ ፓኬጆች ላይ ስልጠና በመስጠትና የስራ ዕድል በመፍጠር ገቢያቸውን እንዲያሳድጉና የኑሮ ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።
ሴክተሩ ለማህበራዊ ልማት የሚኖረውን ሚና ከግንዛቤ በማስገባት ለክህሎት መር የስራ እድል ፈጠራ ቅድሚያ መሰጠቱንም የገለፁት ኃለፊው፥ በተቋሙ የሚስተዋሉ የአሰራር ዉስንነቶችን በዘላቂነት በመፍታት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል አሰራር ይዘረጋል ብለዋል።
የሚስተዋሉ የአሰራር ዉስንነቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል አሰራርን በመዘርጋት ለዘርፉ ዉጤታማነት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ የገለፁት የቢሮው ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ፥ የስራ እድል ፈጠራ ኢኮኖሚን በማነቃቃት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት በመሆኑ፥ በዘርፉ ያለውን ሀብት ተጠቅሞ ኢንቨስትመንት ላይ እንዲዉል በማድረግ ሁለንተናዊ ለዉጥ እንዲረጋገጥ ያግዛል ብለዋል፡፡
በክልሉ በገጠርና በከተማ ወጣቶችን በስራ እድል ፈጠራና ልማት ፕሮግራም በማደራጀት የክህሎት ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ ከፍተኛ ካፒታል በመመደብ ከ 672 ሺህ 600 በላይ ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቁመው፥ በከተማና በአነስተኛና መካከለኛ የአምራች ኢንደስትሪ ዘርፍ ከ 24 ሺህ 500 በላይ ወጣቶችን በማደራጀት ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
መሰረተ ልማት የተሟላላቸውን ምቹ የማምረቻና የመሸጫ ሼዶችን በመገንባት ደረጃቸውን ታሳቢ ያደረገ 3 ሺህ 172 ሼዶችን ለማህበራት ማስተላለፍ መቻሉን የገለፁት አቶ ሙስጠፋ፥ በዚህም ከ 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ ብድር ማሰራጨት መቻሉንም አሰረድተዋል፡፡
በ 2017 በጀት ዓመት የክልሉን አቅም መሰረት ባደረጉ የስራ መስኮች ላይ ከ 3 መቶ 50 ሺህ በላይ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ገልፀው፥ የወጣቶችን ምርታማነት ለማሳደግ የለሙ የወል መሬቶችን፣ የእምነትና የሐይማኖት ተቋማት፣ የጤናና የገበሬ ማሰልጠኛ ተቋማትን በወጣቱ እንዲለማ ለማድረግ መታቀዱን ገልፀዋል፡፡
በጉባኤው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው፣ የክልሉ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ፣ የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አቡቶ አኒቶ፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ኤርሲኖ አቡሬ፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አንተነህ ፈቃዱ፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክላስተር አስተባባሪዎች፣ የቢሮ ኃላፊዎች፣ የዞንና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪዎች፣ የስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ የመዋቅሩ አመራሮች እየተሳተፉ ነው።
ዘጋቢ፡ ዘላለም ተስፋዬ
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ