የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት በማጠናከር ልዩ ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማገዝ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወራቤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አስታወቀ
ኮሌጁ ለ37 አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ በተለያዩ የሙያ መስኮች እያሰለጠነ ይገኛል።
የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጆች በመካከለኛ እና በዝቅተኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ለገበያው ከማቅረብ በተጨማሪ ችግር ፈቺ የሆኑ የቴክኖሎጂ ዉጤቶችን በመፍጠርና በማስተዋወቅ ለማህበረሰቡ የማቅረብ ስራዎችን የሚሰሩ መሆናቸው ይታወቃል።
የወራቤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በተለያዩ የሙያ መስኮች ተማሪዎችን ተቀብሎ ከማስተማር ጎን ለጎን በሚሰጠው የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ልዩ ድጋፍ ለሚሹ አካል ጉዳተኞች የመኖሪያ ቤት፣ የምግብ፣ የትምህርት ወጪ በመሸፈን በኮሌጁ በሚሰጡ የተለያዩ የሙያ መስኮች እያሰለጠነ እንደሚገኝ የተናገሩት የወራቤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ምክትል ዲን እና አካዳሚክ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ከድር ከጄላ ናቸው።
በኮሌጁ ድጋፍ ስልጠናቸውን ከሚከታተሉት ከ37 በላይ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች በተጨማሪ አቅመ ደካማ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት በተለያዩ ጊዜያት የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን እንደሚያደርግ አቶ ከድር ተናግረዋል።
በኮሌጁ ድጋፍ የተደረገላቸውና ቅጥር ግቢው ውስጥ ስልጠናቸውን ያጠናቀቁ አካል ጉዳተኞች በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ተቋማት እያገለገሉ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
ዙለይካ አብረር፣ መሀመድ ከድር እና አብድረዛቅ ሌገሶ ከዞኑ ከተለያዩ አካበቢዎች የመጡና በኮሌጁ በተለያዩ የሙያ መስኮች ስልጣናቸውን እየተከታተሉ ከሚገኙ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች መካከል ተጠቃሽ ሲሆኑ ኮሌጁ ባዘጋጀላቸው የመኖሪያ ቤት ኑሯቸውን በማድረግ ስልጠናቸውን በመከታተል ላይ መሆናቸውን ተነግረዋል።
በኮሌጁ ውስጥ በሚሰሩ በግብርና፣ በዶሮ እርባታ፣ በችግኝ እንክብካቤ የስራ ዘርፎች በመሰማራት ተጠቀሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልፀው ኮሌጁ ለሚያደርግለቸው ሁሉዐቀፍ ድጋፍ አመስግነዋል።
አካል ጉዳተኞች እንደማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ተገቢውን ስልጠናና ድጋፍ ካገኙ ስራ ፈጣሪ፣ አምራችና አገልጋይ መሆናቸውን የሚያነሱት በኮሌጁ የHIV ጉዳዮች በለሙያ የሆኑት ወይዘሮ ሙኒራ ኦርማንጎ፤ አካል ጉዳተኞች ጤናቸው ተጠብቆ ውጤታማ እንዲሆኑ ኮሌጁ የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርግላቸው ተናግረዋል።
መሰል ተቋማት ከተቋቋሙበት ዓላማ በተጓዳኝ መሰል የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶችን በማስፋት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዘጋቢ: ሙጅብ ጁሃር – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
አጀንዳዎችን በማሰባሰብ የህዝቡ ጥያቄ በተገቢው እንዲመለስ የምክክሩ ሂደቱ የላቀ አስተዋፅኦ እንዳለው ተሳታፊዎች ገለፁ
እንደሀገር ካለንበት ችግሮች ወጥተን ዜጎች ተረጋግተው የሚኖሩባት ሀገር እንድትሆን ምክክሩ እንደሚያግዝ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊ አካል ጉዳተኞች ተናገሩ
የጂንካ ዩኒቨርስቲ ለኤሶል ልዩ አዳሪ ትምህርት የተለያዩ ድጋፎችን አደረገ