በጀትን ለታለመለት ዓላማ ብቻ በማዋል ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ልማትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ጥቅምት 16/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጀትን ለታለመለት ዓላማ ብቻ በማዋል ፈጣንና ቀጣይነት ያለውን የዜጎች ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት አመርቂ ውጤት ማስመዝገባቸውን የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ሴክቶሪያል ጉባዔውን በወልቂጤ ከተማ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ ተገኝተው የስራ መመሪያ የሰጡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው፥ የገቢ መሠረቶችን በማስፋትና አቅምን አሟጦ በመጠቀም፥ ሁሉም የሚመለከተው አመራር በገቢ አሠባሰብ ሊሳተፉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
አዳዲስ አሠራርና ሃሳቦችን በማስገባት ያልተሞከሩ ነገሮችን በማካተት፥ የወጡ አዋጆችና ደንቦችን ታሳቢ በማድረግ መስራት ከጠባቂነት በመላቀቅ ስራዎችን በፋይናንስና በገቢዎች ዙሪያ አቅምን አሞጦ መስራት ይገባል ብለዋል።
በተለያየ መንገድ ያገኘነውን ገንዘብ በቁጠባ መጠቀምና ሀብትን በአግባቡ ማስተዳደር እንደሚገባ ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ እያንዳንዱ መዋቅር ዕዳ በማስመለስ፣ ገቢ በመሰብሰብ፣ ወጪን በመቆጠብና ብክነትን በማስወገድ እራሱን መቻል አለበት ብለዋል።
ከዚህ በተጓዳኝ ቅንጅትና ጠንካራ አመራር በመስጠት ሊሰራ እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ መመሪያ ሰጥተዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ የትንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ሃላፊ በበኩላቸው፥ የፋይናንስ ተቋማት ለስትራቴጂክ እቅድ አተገባበርና ለውሳኔ አሰጣጥ፣ ዕድገትንና ዘላቂነትን ለማምጣት መሠረታዊ መርሆዎችና አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰበ በመጣው የኢኮኖሚ ከባቢ ላይ ያለው ድርሻ የጎላ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል የዜጎችን እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት አመርቂ ውጤት መመዝገቡን የጠቆሙት ኃላፊው፥ በወቅታዊነት ላይ የተመሰረተ ዘመናዊ የሂሳብ አያያዝን ተግባራዊ በማድረግ የሀብት ብክነትን መቆጣጠር መቻሉን ገልጸዋል።
በ2016 በጀት ዓመት በጥሬ ገንዘብ አስተዳደር የሚስተዋሉ ብልሽቶችና በመንግሥት ሂሳብ አያያዝ ሪፖርት ወቅታዊነት ጥራት ጋር የተስተዋሉ ጉድለቶች ሊታረሙ እንደሚገባ አመላክተው፥ በ2017 በጀት ዓመት ወጪን የመቀነስ ባህልን በማሳደግ የመንግስትን ሀብት ለታለመለት ዓላማ ብቻ ማዋል እንደሚገባ አሳስበዋል።
የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዘይቱና ኢብራሂም በበኩላቸው፥ ቢሮው በርካታ ተግዳሮቶችን ተሻግሮ ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት ተጨባጭ ውጤት ማምጣት መቻላቸውን ጠቅሰው፥ ያለውን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም በክልሉ ሁለንተናዊ ልማትና ፍትሐዊነት እንዲረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡
ክልሉ ሲመሠረት ሀብትን ብቻ ሳይሆን በርካታ ያደሩ እዳዎችን ተረክቦ እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊዋ፥ ነገር ግን እነዚህን እዳዎች ወደ ምንዳ በመቀየር በጠንካራ ፖለቲካዊ አመራርና ከፍተኛ ጥረት የተረጋጋ፣ ሰላማዊና የህዝቦችን ጥያቄ ለመመለስ የሚሰራ ክልል መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ ዘላለም ተስፋዬ
More Stories
በከተሞች የሚስተዋሉትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ሰፊ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ
ማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡ በመምራት እና በመጠቀም የአካባቢን ገጽታ መገንባት እንደሚገባ ተጠቆመ
የአዳሪ ትምህርት ቤቶች መስፋፋት ጥራት ያለው ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት እንደሚያስችል ተገለጸ