በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተጀመሩ የመስኖ ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ በማድረግ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለፀ
በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት እየተገነቡ በሚገኙ የመስኖ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ ትኩረት ያደረገ የምክክር መድረክ በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የርዕሰ መስተዳድሩ የመሰረተ ልማት ዘርፍ አማካሪ አቶ መዝረዲን ሁሴን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በክልሉ የተጀመሩ የመስኖ ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ እና ጥራት እንዲጠናቀቁ በማድረግ የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ይገኛል፡፡
በክልሉ የተለያዩ የመስኖ አውታሮች ግንባታ እየተከናወኑ ስለመሆናቸው የገለፁት አቶ መዝረዲን፤ አርሶ አደሩ በአመት ሶስት ጊዜ ማምረት እንዲችል በትኩረት መስራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
የመስኖ ልማት ግንባታዎች የሀገሪቱን የልማት እድገት የሚወስኑ በመሆናቸው ይህንኑ እውን ለማድረግ የክልሉ መስኖ ተቋማት ልማት እና አስተዳደር ኤጀንሲ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየሰራ ስለመሆኑ አቶ መዝረዲን ተናግረዋል።
የምግብ ዋስትና በግለሰብ እና በቤተሰብ ደረጃ ማረጋገጥ፣ ተኪ ምርቶችን በጥራት እና በስፋት ማምረት እንዲሁም ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ማቅረብ የክልሉ መንግስት አብይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንና ይህንንም አውን ለማድረግ በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አቶ መዝረዲን አስገንዝበዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመስኖ ተቋማት ልማት እና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ካሳዬ ተክሌ በበኩላቸው፤ ተቋማቸው በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት እየተገነቡ የሚገኙ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ እና ጥራት እንዲጠናቀቁ ለማስቻል መድረኩ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመው በዘርፉ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የመጀመሪያው ሩብ አመት የክረምት ወራት መሆናቸውን ተከትሎ በግንባታ ስራዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደነበረው የተናገሩት ዋና ስራ አስኪያጁ፤ በቀጣዮቹ ወራት በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም አብራርተዋል።
ለመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ስኬታማነት የአማካሪዎች፣ የተቋራጮች፣ እና የማህበረሰቡ እንዲሁም የአሰሪ መስሪያ ቤቱ የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል ኢንጂነር ካሳዬ።
ተቋራጮች ፕሮጀክቶች ሲዘገዩ በመንግስት በጀት ላይ ከሚያደርሱት ኪሳራ ባለፈ የመልካም አስተዳደር ችግር እንደሚያስከትሉ ተገንዝበው ሀላፊነታቸው በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል ሀላፊው፡፡
ተቋራጮች ፕሮጀክቶችን በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ እና ጥራት ሲያጠናቅቁ ፋይዳው ለራሳቸው ነው ያሉት የመድረኩ ተሳታፊ፤ የፕሮጀክት ተቋራጮች እና አማካሪዎች የአየር ሁኔታ እና የመሬት አቀማመጥን ጨምሮ በአንዳንድ ተፈጥሯዊ እንዲሁም ሰው ሰራሽ ችግሮች የተጓተቱ ስራዎች በአጭር ጊዜ ጥራታቸውን በመጠበቅ ሰርተው ለማጠናቀቅ በቅንጅት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ሪድዋን ሰፋ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
አጀንዳዎችን በማሰባሰብ የህዝቡ ጥያቄ በተገቢው እንዲመለስ የምክክሩ ሂደቱ የላቀ አስተዋፅኦ እንዳለው ተሳታፊዎች ገለፁ
እንደሀገር ካለንበት ችግሮች ወጥተን ዜጎች ተረጋግተው የሚኖሩባት ሀገር እንድትሆን ምክክሩ እንደሚያግዝ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊ አካል ጉዳተኞች ተናገሩ
የጂንካ ዩኒቨርስቲ ለኤሶል ልዩ አዳሪ ትምህርት የተለያዩ ድጋፎችን አደረገ