በ19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ላይ የሚታደሙ እንግዶች በከተማው አይረሴ ጊዜን እንዲያሳልፉ እየሰሩ እንደሆነ በአርባምንጭ ከተማ በሆቴል ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ገለፁ
የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት በከተማው ዘመናዊና ጠንካራ የሆቴልና ቱሪዝም ሴክተር ለመገንባት እየተሰራ ይገኛል ብሏል።
በአርባምንጭ ከተማ በልማታዊ ባለሀብቶች የተገነቡ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እየተበራከቱ መምጣትን ተከትሎ የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገር ጎብኚዎች እየተጨመሩ መምጣታቸው ተጠቁሟል።
ይህንንም ተከትሎ ከተማው የተለያዩ ሀገራዊና ክልላዊ ጉባኤዎችንና ስልጠናዎችን እንዲያስተናግድ እድል ፈጥሮለታል ተብሏል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አዘጋጅነት በአርባምንጭ ከተማ የሚዘጋጀው 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን ለማድመቅ የቅድመ ዝግጅት ስራ እያከናወኑ እንደሚገኙ የሀይሌ ሪዞርት አርባምንጭ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት ታሪኩ እና የዳሮስ ሆቴል ባለቤት አቶ ብርሀኑ ዋሬ ይናገራሉ።
እንደእነሱ ገለፃ ከሆነ የአርባምንጭ ከተማ በበርካታ ባህላዊ፣ ሀይማኖታዊ፣ ተፈጥሮአዊና መልከዓ ምድራዊ ፀጋዎች የበለፀገ በመሆኑ 19ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓልን ለማክበር የሚመጡ እንግዶች በከተማው ጥሩ ጊዜ እንዲያሳልፉ የበኩላቸውን ይወጣሉ።
የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት የከተሞች ቱሪዝም አገልግሎት ብቃት ማረጋገጥ ቡድን መሪ አቶ ባህሩ በዙ፤ ከተማው በአባያና ጫሞ፣ በነጭሳርና በዓዞ እርባታ፣ በአርባምንጭ ጥብቅ ደን እንዲሁም በአርባዎቹ ምንጮች የሚታወቅ መሆኑን አውስተው ዘመናዊ የሆቴልና ቱሪዝም ሴክተር በከተማው እየተገነባ ይገኛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን በደማቅ ሁኔታ በከተማው ከማክበር ባለፈ እንግዶች ምቹ በሆነ መንገድ እንዲስተናገዱ ጽ/ቤቱ ከሆቴሎች ጋር በጋራ እየሰራ እንዳለ የገለፁት አቶ ባህሩ የቅድመ ዝግጅት ስራውም እየተጠናቀቀ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
አጀንዳዎችን በማሰባሰብ የህዝቡ ጥያቄ በተገቢው እንዲመለስ የምክክሩ ሂደቱ የላቀ አስተዋፅኦ እንዳለው ተሳታፊዎች ገለፁ
እንደሀገር ካለንበት ችግሮች ወጥተን ዜጎች ተረጋግተው የሚኖሩባት ሀገር እንድትሆን ምክክሩ እንደሚያግዝ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊ አካል ጉዳተኞች ተናገሩ
የጂንካ ዩኒቨርስቲ ለኤሶል ልዩ አዳሪ ትምህርት የተለያዩ ድጋፎችን አደረገ