በዞኑ ሰላም እንዲረጋገጥ ሁሉም አካላት ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለባቸው የጉራጌ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ አስታወቀ
መምሪያው የ2017 ዓ.ም 1ኛ ሩብ አመት የዜጎች ቻርተር ላይ ውይይት አካሂዷል።
የጉራጌ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ሀላፊ ተወካይ አቶ አብርሀም ሞሼ እንደገለጹት የዞኑን ሰላም ለማረጋገጥ ከአጎራባች መዋቅሮች ጋር በመሆን እየተሰራ ነው።
በዞኑ እየተስተዋሉ ያሉ የጸጥታ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዉ፤ የጸጥታ ስጋት ያለባቸው አካባቢዎችን በመለየት ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት አስፈላጊውን የጸጥታ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
የዞኑን ሰላም ለማረጋገጥ ከሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከወጣቶችና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ያሉት ተወካዩ፤ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለባቸም አሳስበዋል።
በዞኑ በወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስራ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት በትኩረት እየተሰሩ መሆኑና ለስራው ውጤታማነትም የሰለጠነ የሰው ሀይል ለማፍራት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እየተሰራ ነው ብለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየትም በዞኑ ያለውን አንጻራዊ ሰላም በማስጠበቅ ለግጭት መንስኤ በሚሆኑ ጉዳዮች ላይ የጸጥታ ችግሮች ከመከሰታቸው አስቀድሞ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የዞኑን ሰላም ማስጠበቅ ከጸጥታው መዋቅር ጋር በመሆን ሌሎች መዋቅሮችና የሀይማኖት ተቋማትን ጨምሮ በዞኑ ሰላም እንዲሰፍን መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በዞኑ በወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስራ ላይ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግና ባለጉዳዮች መጉላላት እንዳይገጥማቸው ከቀበሌ ጀምሮ ባሉ ተግባራት ላይ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጨምረው ገልጸዋል።
በመድረኩ የህዝብ ባለድርሻ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡ መላኩ ንማኒ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት ሥራ ከዳር ለማድረስ በሚደረገው ርብርብ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሙዱላ ከተማ አስተዳደር ገለፀ
በትምህርት ሴክተር የመረጃ አያያዝ ውጤታማነት ዙሪያ በኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
ሁሉንም የመማሪያ መጻሕፍት ባለማግኘታቸው በትምህርታቸው ላይ ጫና እየፈጠረባቸው መሆኑን በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ የቆንጋና ቆቄ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተናገሩ