በሀገር አቀፍና በክልል ደረጃ የተጀመረውን የሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ፍኖተ ካርታ የሁሉ ነገር ማጠንጠኛ ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ

በሀገር አቀፍና በክልል ደረጃ የተጀመረውን የሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ፍኖተ ካርታ የሁሉ ነገር ማጠንጠኛ ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 15/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሀገር አቀፍና በክልል ደረጃ የተጀመረው የሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ፍኖተ ካርታ የሁሉ ነገር ማጠንጠኛ ሊሆን እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ገለጹ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ሴክቶሪያል ጉባኤ የማጠቃለያ መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ብቃት ያለው ሲቪል ሰርቫንት ለመገንባት የሚያስችሉ የሪፎርም ስራዎችን አጠናክሮ መያዝ እንደሚገባ ጠቁመው፥ በዝግጅት፣ በተግባርና በማጽኛ ምዕራፍ የተቀመጡ የለውጥ ስራዎችን አሟልቶ መፈጸም ይገባል ብለዋል።

የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታትና ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዙ መጉላላቶችን መቀነስና የቅሬታ ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ ክፍተቶችን ማረም እንደሚገባ አሳስበዋል።

ብቃት ያለው ሲቪል ሰርቪስ ግንባታ የሚጀመረው ከአገልጋይነት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ስራዎችን ከማስተጓጎል ይልቅ አገልግሎትን በአግባቡ ማቅረብና የተገልጋዩን ፍላጎት በሚያሳኩ ተግባራት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ተቋማት በቅንጅት ሊሰሩና ሴክተር መስሪያ ቤቶች ከሴክተሮች ጋር የጋራ የግንኙነት አግባብ መስርተው መቀናጀት አስፈላጊ መሆኑን አሳስበው፥ የምዘና፣ የማትጊያና የእውቅና አሰጣጥ የአሠራር ስርዓት ሊበጅለት ይገባል ብለዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ በበኩላቸው፥ ከአገልግሎት አሰጣጥ አንጻር ህዝቡ መብትና ግዴታውን ለይቶ የሚያውቅ ከመሆኑም በላይ፥ ሲቪል ሰርቫንቱ በዛው ልክ የማገልገልና የማስተናገድ አቅሙን ማሳደግ እንደሚገባ አመላክተዋል።

ከሰራተኛ ቅጥር፣ ዝውውር፣ የደረጃ እድገትና በአንድ መደብ ላይ ደራርቦ ቅጥር ከመፈጸም ጋር ተያይዞ ያሉ ብልሹ አሰራሮችንና ሙስናን ማረምና መታገል ያስፈልጋል ብለዋል።

የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ገብሬ ጋጌ፥ ከሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ማጣራት ጋር ተያይዞ 73 ሃሰተኛ ዲግሪና 197 የC.O.C የብቃት ማረጋገጫ በምርመራ መያዛቸውን ጠቁመው፥ ተጨማሪ 70 ሺህ 233 ዲግሪና ከዚያ በላይ ያሉ የትምህርት ማስረጃዎችን ለማጣራት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በቀረበው የውይይት ሰነድ ላይ ከተሳታፊዎች ሃሳብና አስተያየት የተሠጠበት ሲሆን፥ ከመድረኩ ምላሽና ማብራሪያ ቀርቦበት የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ የጉባኤው ማጠቃለያ ሆኗል።

ዘጋቢ፡ ዘላለም ተስፋዬ