በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባለው የኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ እመርታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ምክክር እየተካሄደ ነው

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባለው የኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ እመርታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ምክክር እየተካሄደ ነው

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 14/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባለው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ላይ እመርታዊ ለውጥ ለማምጣት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ክልሉ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስራ አስፈጻሚዎች ጋር በጋራ እየመከረ ነው።

በምክክሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው፥ በዘርፉ በክልሉ ከፍተኛ ተግባራት መከናወኑን ጠቁመው፥ በዚህም የተመዘገቡ ውጤቶች ስለመኖራቸው ተናግረዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች ችግር ያጋጠማቸው ፕሮጀክቶች መኖሩን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ አዳዲስ የሃይል ፍላጎት በከተማም ሆነ በገጠር እያደገ መምጣቱን ገልጸው፥ ነገር ግን በአገልግሎቱ ንብረት አያያዝና አጠቃቀም ላይ የሚያጋጥሙ ውስንነቶችን ለይቶ መፍታት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ምክክሩ በክልሉ ያለውን የሃይል አቅርቦት ለማሻሻልና ያጋጠሙ ችግሮችን በጋራ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በቅንጅት ተባብሮ ለመስራትና ክፍተቶችን ለይቶ ለመፍታት ያግዛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጅነር ሽፈራው ተሊላ በበኩላቸው፤ ኮርፖሬሽኑ አዲስ የሪፎርም ስራ በመጀመር ተቋማዊ ለውጥ በማድረግ ላይ መሆኑን ገልፀዋል።

ምክክሩ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጋር ያለውን ትስስር ለማጠናከር እና ስራዎችን በጋራ ለመስራት ያስችላል ብለዋል።

በህብረተሰቡ ለሚነሱ የመብራት ተደራሽነት ጥያቄ በምክክሩ ምላሽ ለመስጠት እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፥ የአገልግሎቱን ተደራሽነት ለማስፋት ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የሚሰሩ የተለያዩ ስራዎች መጀመራቸውን አስረድተዋል።

ህብረተሰቡ መሰረተ ልማቶችን ተንከባክቦ በመያዝ እና በመጠበቅ ሰው ሰራሽ በሆኑ ምክንያቶች የሚፈጠሩ የኃይል መቆራረጦች እንዳይኖሩ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ኃላፊው አሳስበዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የካቢኔ አባላትና የዞን አስተዳዳሪዎች፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የቅርንጫፍ ስራ አስኪያጆች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ ዘላለም ተስፋዬ