የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ከብሪጅ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን ድርጅት ጋር በትራንስፖርት ዘርፍ በዲጂታል ኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት ዙሪያ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የውል ስምምነት ተፈራረሙ

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ከብሪጅ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን ድርጅት ጋር በትራንስፖርት ዘርፍ በዲጂታል ኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት ዙሪያ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የውል ስምምነት ተፈራረሙ

በወልቂጤና ሆሳዕና መናኸሪያዎች የሚተገበረው የዲጂታል ኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት የተገልጋዩ ህብረተሰብ ተጠቃሚነትን ይበልጥ ለማሳደግ ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም ተመላክቷል።

በውል ስምምነቱ ወቅት የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ምክትልና የትራንስፖርት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ሰንበቶ አባባ እንደገለፁት በተለይም በመናኸሪያዎች አካባቢ ከአገልግሎት አሰጣጥ አንፃር የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ የዲጂታል ኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት ትልቅ ፋይዳ እንዳለውና በክልሉ ከዚህ ቀደም በወልቂጤና በሆሳዕና መናኸሪያዎች የሙከራ ትግበራ ሲከናወን ቆይቷል።

በሁለቱም ከተሞች መናኸሪያዎች በኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት የሙከራ ትግበራ ወቅት የተደረገው የውል ስምምነት የጊዜ ገደብ እየተገባደደ መምጣቱን ተከትሎ የወቅቱን ታሪፍ መነሻ በማድረግ በቀጣይ በጋራ መሥራት የሚያስችል የውል ስምምነት ከብሪጅ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን ድርጅት ጋር መፈራረማቸውን አስረድተዋል።

አሁን ላይ የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎቱን በክልሉ በሚገኙ 7 መናኸሪያዎች የሙከራ ትግበራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የጠቆሙት ሀላፊው ቴክኖሎጂው በተለይም የትራንስፖርት ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥን ፈጣንና ቀልጣፋ እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ነው ያሉት።

አገልግሎቱ ከታሪፍ በላይ ማስከፈልን እያሰቀረ ከመምጣቱ ባለፈም ለዘርፉ አጋዥ የሆኑ ሌሎች መረጃዎችን ለማግኘት ዕድል በመፍጠር ረገድ ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ተገልጋዩ ህብረተሰብ ከመናኸሪያ ውጪ ሌላ ተጨማሪ ክፍያ የሌለ መሆኑን አውቆ እንዲተገብር ያነሱት ሀላፊው ለዚህም አስፈላጊውን የቁጥጥርና ክትትል ሥራ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ እንደሆነ አመላክተዋል።

በተለይም ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት መስጠት ወሳኝ መሆኑን ያመላከቱት አቶ ሰንበቶ በመሆኑም ብሪጅ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን ድርጅት በገባው ውል መሠረት የተጣለበትን ሀላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የብሪጅ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን ድርጅት ተወካይና አማካሪ አቶ እሸቱ አየለ እንዳሉት ድርጅታቸው የተለያዩ የሶፍት ዌር ውጤቶችን ለመንግስት እና ለግል ተቋማት እንደሚያቀርብ በመጥቀስ በዚህም አሁን ላይ ከ500 በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።

ቴክኖሎጂው በክልሉ በመተግበሩ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡን ከማዘመን በዘለለ አስፈላጊውን መረጃ ተደራሽ ማድረግ የሚቻልበት ዕድል መፍጠሩን ገልፀዋል።

ቴክኖሎጂው በሆሳዕና እና ወልቂጤ ከተሞች ይበልጥ በማዘመን ተግባራዊ ለማድረግ ከስምምነት መደረሱን በመጥቀስ ስራው በገቡት ውል መሠረት ለመፈጸም ድርጅታቸው አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቀዋል።

ዘጋቢ፡ መሀመድ ሽሁር – ከወልቂጤ ጣቢያችን