“አካል ጉዳተኝነት ባለመቻል ውስጥ የምታሳየው መቻል ነው” – ወ/ሪት የአብስራ ፍሬው

በገነት ደጉ

የዛሬዋ ባለታሪካችን ወ/ሪት የአብስራ ፍሬው ትባላለች፡፡ ነዋሪነቷ ሀዋሳ ከተማ በተለምዶ አቶቴ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ ዩኤስ ተብሎ በሚጠራ ግብረሰናይ ድርጅት ውስጥ የስራ አጥ ወጣቶች አማካሪ (ዩዝ አድቫይዘር) በመሆን ተቀጥራ እየሰራች ትገኛለች፡፡

ትውልድ እና እድገቷ በሲዳማ ክልል አለታ ጩኮ በሚባል አካባቢ ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በአለታ ጩኮ መካነ-ኢየሱስ ሚሲዮን ትምህርት ቤት ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ ተከታትላለች፡፡

ከ9ኛ እስከ 10ኛ ክፍል ትምህርቷን ደግሞ በአለታ ወንዶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስትከታተል ቆይታ፤ የ11ኛ እና የ12ኛ ክፍል ትምህርቷን በአለታ ወንዶ ጃፓን ተብሎ በሚጠራው የመንግስት ትምህርት ቤት ማጠናቀቋን ነው ያጫወተችን፡፡

በ2011 ዓ.ም በጥሩ ውጤት ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች የምትናገረው የአብስራ፤ በወቅቱ በትምህርት ቤቱ ካሉ ሴቶችም ሆነ አካል ጉዳተኞች የተሻለ ውጤት ማምጣቷ በራስ የመተማመን አቅሟን ይበልጥ እንዳሳደገላት እና ጀግንነት እንዲሰማት እንዳደረጋት ታስታውሳለች፡፡

ወ/ሪት የአብስራ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሚያስገባትን ውጤት አምጥታ ተመድባለች፡፡ በመሆኑም በምደባ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ቢደርሳትም የአብስራን የሚያግዛት ሰው ኢንፎሊንክ ዩኒቨርሲቲ ስለነበር እና ነፃ የትምህርት ዕድልም እንዳላቸው መረጃውን በማግኘቷ ምርጫዋን ሀዋሳ በሚገኘው ኢንፎሊንክ ዩኒቪርሲቲ ኮሌጅ አደረገች፡፡

በኢንፎሊንክ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመደበኛ ፕሮግራም ትምህርቷን ለአራት ተከታታይ ዓመታት ስትከታተል ቆይታ በ2015 ዓ.ም 3 ነጥብ 9 በማምጣት በከፍተኛ ማዕረግ መመረቅ ቻለች፡፡ ለዚህም የረዳት ዓላማዋን ጠንቅቃ በማወቋ ቅድሚያ ለትምህርቷ መስጠቷ እንደሆነ ታነሳለች።

“አካል ጉዳተኝነት እኔን ጠንካራ አድርጎኛል” የምትለው የአብስራ “የተፈጠርሽበት ዓላማ ትርጉሙ ሲገባሽ ለምታደርጊያቸው ነገሮች ራስሽን አሳልፈሽ መስጠት አለብሽ” ትላለች፡፡

ለትምህርቷ በቂ ትኩረት እና ጊዜዋን በመስጠት የተሻለ ደረጃ መድረስ ስለመቻሏ የምትናገረው መንፈሰ ጠንካራዋ የአብስራ ዓላማዋን ለማሳካት ጥረት ባታደርግ ኖሮ በሁለት እጆቿ ላይ በደረሰባት የአካል ጉዳት ምክንያት እቤት ውስጥ ልትቀር እንደምትችልም ሳታነሳ አላለፈችም፡፡

የሁለቱ እጆቿ መጎዳት ማንኛውም ሰው ሊሰራ ከሚችለው ስራዎች እንዳልገደባትም። ተወልዳ ባደገችበት አካባቢ የነበረው ተጽዕኖ አሁን የደረሰችበት ቦታ ሊያደርሳት እንደማይችል መለስ ብላ በማስታወስ ትኮንነዋለች። በወቅቱ ለራሷ የሰጠችው ቦታ ዝቅተኛ እንደነበር እና ከጊዜ ወደ ጊዜ (እየበሰለች ስትመጣ) አመለካከቷን በመቀየር የተሻለ ደረጃ ላይ መድረሷን ትናገራለች፡፡

አካል ጉዳተኝነት በተፈጥሮ የደረሰባት ባለታሪካችን “አካል ጉዳተኝነት አለመቻል ሳይሆን ባለመቻል ውስጥ የምታሳይው መቻል ነው” ስትል የጥንካሬዋን ጥግ ትገልፃለች፡፡

አንዳንድ አካል ጉዳተኞች መስራትና መለወጥ እንደሚችሉ አምነው ባለመቀበላቸው በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ አካል ጉዳተኝነት እርግማን አይደለም የምትለው የአብስራ፤ ፈጣሪ ሁሉንም ሰዎች በፈጠረው ልክ እኔም ተፈጥሬያለሁ የሚል የፀና እምነት አላት፡፡

በተለይ ተመሳሳይ ማንነት ባላቸው ሰዎች መካከል የተለየ ሆና እንደምትታይ ታነሳለች፡፡ “በቤተሰቦቼ ድጋፍ ነው እዚህ መድረስ የቻልኩት። ቤተሰቦቼ ጉዳቴን አምነው በመቀበል ለብዙ ሰዎች እንድተርፍ አድርገው ነው ያሳደጉኝ፡፡ በእነሱም ድጋፍ በህይወቴ ትልቅ እና አስከፊውን ጊዜ አሳልፌያለሁ፡፡

“ከገጠር ወደ ከተማ በምወጣበት ወቅት በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ አምኖ አለመቀበል በስፋት ያጋጥመኝ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ሰዎች ያገልሉኝ ነበር፡፡

“ከሰዎች ጋር በመቀራረብ ነው ለውጥ የሚመጣው፡፡ እነሱም ካራቁኝ እኔም ከራቅኩ መግባባት አይቻልም፡፡ ይህንን ሀሳብ ይዤ ነው ዛሬ ላይ የደረስኩት፡፡” በማለት ያጋጠሟትን ፈተናዎች እና ያለፈችበትን መንገድ፣ እንዲሁም ከሰዎች ጋር የነበራትን የተግባቦት ሂደት አስረድታለች፡፡

አክላም፡- “በማትጠብቂው ሰው ብዙ ልትጎጂ ትቺያለሽ፡፡ በጣም የሚጎዳሽ ግን የምታውቂው ሰው ሲያገልሽ ነው፡፡ በእኔም ሕይወት የተፈጠረው እንደዚህ ዓይነት አጋጣሚ ነው፡፡ ባሳለፍኳቸው ጊዜያት ራሴን እንዳልቀበል የሚያደርጉ ሁኔታዎች አጋጥመውኛል፡፡

“ይሁን እንጂ ለህይወት መልካም የሆኑ ነገሮችን ብቻ መስማትና መልካም ያልሆኑ ነገሮችን የማለፍ ልምዴ ብዙ ጠቅሞኛል፡፡ ሰዎች ያሉትን ነገሮች ሁሉ የምሰማ ብሆን የምገኘው የልመና ቦታዎች ላይ ሊሆን ይችል ነበር፡፡ ዛሬ ላይ የደረስኩበት ደረጃ መድረስ የቻልኩት በፈጣሪ ፀጋ እና የሰዎችን ትችት ባለመስማቴ ነው” ብላለች፡፡

“ሁሉም ነገር አልፎ ቀላል ይመስላል እንጂ ከጀርባ ብዙ ተግዳሮቶች ነበሩ” የምትለው ወ/ሪት የአብስራ፣ መልካምነትን የሚያስቀጥሉ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ መልካም ህይወት እንዳይቀጥል የሚያሰናክሉ ሰዎች መኖራቸውንም ሳታነሳ አላለፈችም፡፡

አካል ጉዳተኝነት እና ሴትነት እንዴት ይገለፃል? ብለን ላነሳንላት ጥያቄ እንዲህ ስትል ምላሿን ሰጥታናለች፡- 

“ሴት ሆኜ ሁለት እጅ ማጣቴ በጣም ፈትኖኛል፡፡ ወደ ወጣትነት ዕድሜ ውስጥ በገባሁ ጊዜ ለምን በማለት እራሴን ሁልጊዜ እጠይቅ ነበር፡፡ ይህም በጣም ጎድቶኝ ነበር፡፡ በወጣትነት ዕድሜ ያሳለፍኳቸው ጊዜያትን ማስታወስን አልፈልግም፡፡” ስትል በምሬት ነበር ያጫወተችን፡፡

“በተለይ ራሴን እያወኩኝ ስመጣ ተስፋ የቆረጥኩባቸው ጊዜያቶች ነበሩ፡፡ ከባድና በፈተና የተሞሉ ጊዜያትን ነው ያሳለፍኩት፡፡ በወቅቱ ትክክለኛ ደስታን ላላገኝ እንደምችል ባሰብኳቸው ቦታዎች ሳይሆን ተስፋ በማድረግ ውስጥ ነው ደስታ፣ ዕድል እና ህይወት ያገኘሀት፡፡ በፊት ብዙ ነገሮችን ያለሰው ማድረግ አልችልም ነበር፡፡ አሁን ግን ራሴን ችያለሁ፡፡ ይህ ሁሉ የመነጨው ተስፋ ባለመቁረጤ ነው” በማለት በህይወቷ ያሳለፈችውን የህይወት ተሞክሮ አጋርታናለች፡፡

በምትሰራው ግብረ-ሰናይ ድርጅት በዓመት 175 ሺህ ብር መፈራረሟን የምትናገረው የአብስራ፣ በወር ከ25 ሺህ ብር በላይ ተከፋይ ነች፡፡ በሕይወታችን የሚያጋጥሙን ነገሮች ሁሉ ያልፋሉ። ለዚህ ግን አንድ ነገር ሲከሰት ከማፈግፈግ ይልቅ ጠንካራ በመሆን ከችግሩ ጋር መጋፈጥ ነገን የተሻለ እንደሚያደርግ ነው ያጫወተችን፡፡

“አሁን ላይ ባለሁበት አካባቢ ብዙ ሰዎች በጥንካሬዬ ስለሚያውቁኝ ያበረታቱኛል” የምትለው የአብስራ የሁለተኛ ድግሪዋን በሳይኮሎጂ የትምህርት ዘርፍ ለመማር ዝግጅቷን ማጠናቀቋን ነው ያነገረችን፡፡

ይህች ወጣት ያሳለፈችውን የህይወት ውጣ ውረድ ጠንቅቃ ስለምታውቀው ከመደበኛ ስራዋ ጎን ለጎን ምሳሌ ፋውንዴሽን የሚል በጎ አድራጎት ድርጅት እንዳላት ነግራናለች፡፡ በየዓመቱ ካሉት በዓላት በአንዱ አቅመ ደካሞችንና የጎዳና ልጆችን ምግብ እንደሚያበሉ እና የዚህም በጎ አድራጎት ድርጅት መስራች እንደሆነች ነው የጠቀሰችው፡፡

በተለይም በደብተርና የመማሪያ ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ትምህርታቸውን ለሚያቋርጡ ተማሪዎች አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግም ትታወቃለች፡፡ በያዝነው ዓመትም በየክፍለ ከተማው ደብተርም ሆነ የማዕድ ማጋራት ተግባራትን እንዳከናወኑ ነው የገለፀችው፡፡

በ2015 ዓ.ም ለጎዳና ልጆች እና ደብተር ላጡ ተማሪዎች ድጋፍ ማድረግ ስለመቻላቸው አንስታ በዘንድሮ ዓመትም በየክፍለ ከተማው ችግሩ ላለባቸው ተማሪዎች ለእያንዳንዳቸው አንድ ደርዘን ደብተር እና እስኪቢርቶ መስጠት መቻላቸውን ገልጻለች፡፡

የበጎ አድራጎት ተግባሩን  ከወጣቶች ጋር ከጀመረች ሁለት አመት እንደሞላው የምታስታውሰው ባለታሪካችን በየክፍለ ከተማው የደሃ ደሃ ተብለው ለተለዩ ልጆች ዕድሉን እንደሚሰጡ ነው የጠቀሰችው፡፡

በትልልቅ መድረኮች ወጥታ የራሷን የህይወት ልምድ በማካፈል ስልጠናዎችን ትሰጣለች፡፡ በተለይም በፆታ እኩልነት እና በሴቶች ተሳትፎ ተጠቃሚነት ላይ ተጠርታ ስልጠና እንደምትሰጥ ነው የገለፀችው፡፡

ጊዜዋንና ህይወቷን ለሌሎች ተምሳሌት ለመሆን ከስራዋ ጎን ለጎን ብዙ ስራዎችን ትሰራለች፡፡ በራሷ ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን ዘጋቢ (ዶክመንተሪ) ፊልም በመስራት ሽልማት እና ሰርተፊኬት እንደተበረከተላትም ትናገራለች፡፡

በ2016 ዓ.ም ከዓለም 26ኛ ከኢትዮጵያ ደግሞ ምርጥ ተዋናይ ተብላም ተሸልማለች። ከብዙ አርቲስቶች መካከል መሸለሟ እጅግ እንዳስደሰታት እና ለቀጣይ ስራዋ ስንቅ እንደሆናት ነው ያስረዳችው፡፡

“ብዙውን ጊዜ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆንን እመኝም ነበር፡፡ ያ ካልሆነ ግን ግደለኝ እያልኩ ፈጣሪን እማፀነው ነበር” ስትል ያለፈውን ጊዜ ታስታውሳለች፡፡

በቲክቶክም ላይ “የአብ የጌታ ልጅ” በተሰኘ የግል ገጿ አንዳንድ ስራዎችን እየሰራች ትገኛለች። ብዙዎችም እያበረታቷት እንደሆነ እና ወደ 300 ሺህ የሚሆኑ ተከታዮች እንዳሏት ነው ያጫወተችን፡፡

“በተለይም አካል ጉዳተኞች ብዙ ነገር መስራት ሲችሉ ራሳቸውን አንችልም በማለት ከብዙ ስራዎች ገድበዋል እና ለአካል ጉዳተኞች ሁሉም ይቻላል” በማለት መልዕክቷን አስተላልፋለች፡፡