የከተሞች ፕላን ዝግጅትና አተገባበር ማህበረሰብ ተኮር፣ ዘላቂ ልማትና እድገት ሊያመጣ በሚችል መልኩ መሆን እንዳለበት የኢፌዲሪ ከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ገለፀ

የከተሞች ፕላን ዝግጅትና አተገባበር ማህበረሰብ ተኮር፣ ዘላቂ ልማትና እድገት ሊያመጣ በሚችል መልኩ መሆን እንዳለበት የኢፌዲሪ ከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ገለፀ

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ በከተሞች ፕላን ዝግጅት፣ አተገባበርና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከክልሉ፣ ከዞን፣ ከልዩ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ለተውጣጡ ባለሙያዎችና ለዘርፉ ሃላፊዎች በወልቂጤ ከተማ ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቋል፡፡

በስልጠናው ላይ የተገኙት የኢፌዲሪ ከተማና መሰረተ ልማት ሚንስቴር የከተሞች አከታተም ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ገነት ገ/እግዚአብሔር እንደገለፁት ከተሞችን ለኑሮ ምቹና ተስማሚ እንዲሁም ለኢንቨስትመንት ተመራጭ በማድረግ ዘላቂና የተሻለ መሰረት ልማት ለማከናወን ፕላን ወሳኝ ነው።

በመሆኑም በከተሞች የፕላን ዝግጅትና አተገባበር ወቅቱን በሚመጥንና በተሻለ ቴክኖሎጂ በመታገዝ መተግበር ይገባል ያሉት ወ/ሮ ገነት ለዚህም ውጤታማነት የዘርፉ ባለሙያዎች ክህሎት ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በተለይም የከተሞች ፕላን ማህበረሰብ ተኮር፣ ዘላቂ ልማትና እድገት ሊያመጣ በሚችል መልኩ መከናወን እንዳለበት ሃላፊዋ ገልፀዋል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት የከተማ ፕላን ዝግጅት ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አቶ እሸቱ ካሳ በበኩላቸው ስልጠናው በፕላን ዝግጅትና አተገባበር ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በመቅረፍ የተሻለ ስራ ለመስራት የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።

ይህም የባለሙያውን ቴክኒካል አቅም በማሳደግ ውጤታማ የፕላን ዝግጅትና አተገባበር እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።

ስልጠናው ለቀጣይ ስራቸው አጋዥ ከመሆኑም በተጨማሪ ወቅቱን ያማከለ መሆኑን የስልጠናው ተሳታፊዎች ተናግረዋል።

በተለይም በወቅቱ ቴክኖሎጂ በመታገዘ ጥራቱን የጠበቀና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸው መሆኑን ገልፀዋል።

ዘጋቢ፡ ጅላሉ ፈድሉ – ከወልቂጤ ጣቢያችን