የጥራት መለያ ያለውን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ እንደሚገኝ ተገለጸ

የጥራት መለያ ያለውን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ እንደሚገኝ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 13/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥና የጥራት መለያ ያለውን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ እንደሚገኝ በሀድያ ዞን የግቤ ወረዳ ቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ጽ/ቤት አስታወቀ።

ጽ/ቤቱ በምርቱ ላይ ህገ-ወጥነት እንዳይስፋፋ የተቀናጀ የቁጥጥር ስርዓት መተግበር እንደሚያስፈልግም ጠቁሟል።

የወረዳው ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሸምሰዲን ጀማል፤ በወረዳው የአርሶአደሩን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥና የጥራት መለያ ያለውን ቡና በማምረት ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ከአካባቢው የአየር ንብረት ጋር በተለይም 74-10 እና 74-12 የተሰኙ የቡና ዝርያዎች እጅግ ተስማሚ በመሆኑ አርሶአደሩ በባለሙያው ታግዘው ዝርያውን በማስፋፋት ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሠራ ስለመሆኑም ነው ያመላከቱት።

ኃላፊው አክለውም አርሶአደሩ ምርታማነት የሌላቸውን ነባሩንና የተሻሻለውን የቡና ዝርያዎችን በተገቢው መልኩ ማልማት ከቻለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠቃሚ የሚሆንበት ዕድል ሰፊ ስለመሆኑም አስገንዝበዋል።

በቡና ማሳ ተጨማሪ አዝርዕትንም ይሁን ተክሎችን ባለማቀላቀል መጠበቅ ወሳኝ ነው የሚሉት አቶ ሸምሰዲን ያረጁ የቡና ዛፎችን በመጎንደልና ዳግም እንዲያቆጠቁጥ በማድረግ ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚቻል አስረድተዋል።

አርሶአደሩ የቡና ማሳ ከመንከባከብም በሻገር አልፎ አልፎ የሚከሰት የበሽታ አይነት በተለይም እንደ ግንድ አድርቅ የሚባል ሊኖር ስለሚችል የቅርብ ክትትል በማድረግና የዘርፉን በለሙያዎች በማማከር አስቀድሞ መከላከል እንደሚገባም አሳስበዋል።

ጽ/ቤቱ የዘርፉን ዉጤታማነት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረው ከአዋደ የምርምር ማዕከል ጋር የተጀመሩ ስራዎች ስለመኖራቸውም አመላክተዋል።

ቡና የሀገር ሀብት ነው ያሉት ኃላፊው አቶ ሸምሰዲን በምርቱ ላይ ህገ-ወጥነት እንዳይስፋፋና የምርት ብክነት እንዳይኖር ሁሉአቀፍ የሆነ የቁጥጥር ስርዓት ሊተገበር እንደሚገባም ነው የጠቆሙት።

በወረዳው በሃደዬ እና ዳንሻ ቀበሌያት አግኝተን ያነጋገርናቸው አርሶአደር ኤርዶዕሎ ሲምቦ እና አብርሃም ፍቅሬ፥ በጓሯቸው ቡና ተክሎ መጠቀም ከጀመሩ ረዥም ጊዜያትን ያስቆጠረ መሆኑን በመግለጽ ቀደምሲል በቡና አያያዝና አጠቃቃም ላይ ክፍተቶች እንደነበረባቸው ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ከቅርብ አመታት ወዲህ ከዘርፉ ባለሙያዎች ባገኙት ልምድና እገዛ የቡና ምርታማነት እየተሻሻለ ስለመምጣቱ በመጥቀስ በነባሩም ሆና በተሻሻለው የቡና ዝርያ ያገኙትን የጥቅም ልዩነት ማመዛዘን እንደቻሉም አንስተዋል።

የበለጠ ምርታማነትን ለማረጋገጥ እንዲያስችል በመንግስት በኩል የተጀመረው ሙያዊ እገዛም ይሁን የተሻሻለውን የቡና ችግኝ የማቅረብ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አርሶአደሮቹ ጠይቀዋል።

ዘጋቢ: አለቃል ደስታ – ከሆሳዕና ጣቢያችን