ሀዋሳ፡ ጥቅምት 12/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከወንዝ አሳ በማምረት ለጅምላ ተረካቢዎች በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን በደቡብ ኦሞ ዞን በኛንጋቶም ወረዳ በአሳ ማስገር ተግባር በማህበር የተሰማሩ ወጣቶች ገልጸዋል።
በአሳ ማስገር ሃያ አራት አባላትን ያቀፉ ሁለት ማህበራትን በማሰማራት በሩብ አመቱም ከ5 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ የአሳ ምርት ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ጠቁሟል።
በወረዳው ቻሬ ቀበሌ በማህበር ከተደራጁ ወጣቶች መካከል ወጣት ሞታል ላስቡክ እና ሎኩዋ ቡዳ እንደገለጹት መንግስት 12 አባላትን አሰባስቦ የማምረቻ መረብና ፍሪጅ የመሳሰሉትን አሟልቶ ወጣቶቹ ከኦሞ ወንዝ አሳ በማምረት ለጅምላ ተረካቢዎች በኪሎ በመሸጥ ተጠቃሚ ሆነዋል።
በሦስት ወር ጊዜ ውስጥም 47 ሺህ ብር ያህል ያገኙ ሲሆን ሰሞኑን ወንዙ በመሙላቱ ለማስገር አስቸጋሪ እንደሆነባቸውና በቀጣይ መንግስትና ረጅ አካላት ዘመናዊ ጀልባና ተሽከርካሪ ሞተር ድጋፍ ቢያደረጉላቸው እራሳቸውንም ሆነ ሀገራቸውን ይበልጥ እንደሚጠቅሙ አስረድተዋል።
አሳን ለማዕከላዊ ገበያ የምያቀርቡት የአቶ መሀመድ ሁሴን ባለቤትና ተወካይ ወ/ሮ ማረግነሽ ታደለ እንደገለጹት ማህበራቱ ያመረቱትን አሳ በኪሎ ከ100 እስከ 150 ብር በመረከብ በፍሪጅ በማቀዝቀዝ፣ በማድረቅ ለማዕከላዊ ገበያ ያቀርባሉ።
አሳው የሚመረትበት አካባቢም ከ10 ኪሎ ሜትር በላይ የሚያስኬድ በመሆኑ ምርቱ እንዳይበላሽ ለማህበራቱ ተሽከርካሪ ሞተርና መሰል ድጋፎች ቢደረግ መልካም መሆኑንም አሳስበዋል።
የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት የእንስሳት እርባታና መኖ ልማት የስራ ሂደት ቡድን መሪ አቶ አለማየሁ ዘሪሁን እንደገለጹት በወረዳው በኦሞ ወንዝ ያለውን የአሳ ምርት በማምረት የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በሁለት ቀበሌያት 24 አባላት ያሉትን አስጋሪ ማህበራት በማደራጀት ማስገርያ መረብና ፍሪጅ በማሟላት ወደ ስራ ገብተዋል።
ማህበራቱም ያመረቱትን ምርት ለጅምላ ነጋዴዎች እንደሚያስረክቡና በሩብ አመቱም 5 ሺህ 2 መቶ 83 ኪሎ ግራም የአሳ ምርት ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን ቡድን መሪው አስረድተዋል።
በይበልጥ የዘርፉን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግም ለማህበራቱ የዘመናዊ ጀልባና ተሽከርካሪ ሞተር ድጋፍ በረጂ ድርጅቶችና መንግስት በኩል ለማመቻቸት ጥረት አየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ተመስገን ሰይፉ – ከጂንካ ጣቢያችን

                
                                        
                                        
                                        
                                        
More Stories
እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት ሥራ ከዳር ለማድረስ በሚደረገው ርብርብ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሙዱላ ከተማ አስተዳደር ገለፀ
በትምህርት ሴክተር የመረጃ አያያዝ ውጤታማነት ዙሪያ በኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
ሁሉንም የመማሪያ መጻሕፍት ባለማግኘታቸው በትምህርታቸው ላይ ጫና እየፈጠረባቸው መሆኑን በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ የቆንጋና ቆቄ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተናገሩ