ሀዋሳ፡ ጥቅምት 12/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) አርሶ አደሩ ዝርያቸው የተሻሻሉ የዳልጋ ከብቶችን እንዲያረባ በማድረግ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ ገለጸ።
ዞናዊ የዳልጋ ከብቶች በሆርሞን የማድራት (ሲንክሮናይዜሽን) መርሃ ግብር በዞኑ ጌታ ወረዳ አታዞ ቀበሌ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ አርሶ አደሩ ካለው የመሬት ጥበትና የመኖ አቅርቦት ውስንነት አኳያ ሀገረ-ሰብ ከብቶችን ከማርባት ወጥቶ ዝርያቸውን የተሻሻሉ የዳልጋ ከብቶች እንዲያረባ በማድረግ ሁለንተናዊ ተጠቃሚ እንዲሆን ይሰራል።
በመሆኑም በዞኑ ከ3 ሺህ በላይ የዳልጋ ከብቶችን በሆርሞን በማድራት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ ይሰራል ነው ያሉት።
በዞኑ የወተት አቅርቦት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ያነሱት አቶ አበራ፤ ከህብረተሰቡ ፍላጎት አኳያ የበለጠ አስፍቶ መስራት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።
በዞኑ የፈሳሽ ናይትሮጂን አቅርቦት ችግር መኖሩን ገልጸው ችግሩን ለመቅረፍ ከተለያዩ ማዕከላትና ከሚመለከታቸው አካላት እየተሰራ ያለውን ስራ ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።
አክለውም በዞኑ በሌማት ትሩፋት ተግባራት በተለይም የወተት መንደር ለመፍጠር የተጀመረውን ስራ በማጠናከር ዝርያ ማሻሻል ላይ የተጀመረው ስራ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የዞኑ ግብርና መምሪያ ምክትልና የእንስሳት ዘርፍ ኃላፊ አቶ መሀመድ ሙደሲር በበኩላቸው በዞኑ በመደበኛ፣ በሲንክሮናይዜሽንና በተሻሻለ ኮርማ 28 ሺህ 176 የዳልጋ ከብቶችን ዝርያቸውን በማሻሻል 15 ሺህ 8 መቶ ዝርያቸው የተሻሻሉ ጥጃዎች ለማግኘት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዞኑ ከ2 ሚሊዮን በላይ የቀንድ ከብቶች እንዳሉ ያነሱት ኃላፊው ከእነዚህም ውስጥ እስካሁን 4 መቶ ሺህ የዳልጋ ከብቶች ብቻ ዝርያቸውን ማሻሻል መቻሉን ነው የገለፁት።
በዞኑ የዝርያ ማሻሻል ስራ በትኩረት በመስራት የወተት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ በመጠቆም ይህም አርሶ አደሩ ቀንድ ከመቁጠር በመውጣት ዝርያቸው የተሻሻሉ የወተት ላሞችን በማርባት የምግብ ዋስትናውን ከማረጋገጥ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዲሆን ያደርገዋል ብለዋል።
በዞኑ ከዚህ ቀደም የወተት አቅርቦት ችግር እንደነበር አውስተው በዘርፉ በየደረጃው በተሰራው ስራ አሁን ላይ የወተት አቅርቦቱ መሻሻሉን ያነሱት አቶ መሀመድ፤ ይህንን ተከትሎም በዘንድሮው አመት 80 ሺህ ቶን ሊትር ወተት ለማምረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህ ተግባር ውጤታማነትም በዘንድሮው አመት 8 ሺህ ሄክታር መሬት ዝርያቸው የተሻሻለ መኖ መተከሉንም አመላክተዋል።
የጌታ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀብቱ ወልደ ኢየሱስ የወረዳው አርሶ አደሮች ቀንድ ከመቁጠር በመውጣት ዝርያቸው የተሻሻሉ የዳልጋ ከብቶችን በማርባት ሁለንተናዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይሰራል ብለዋል።
የጌታ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙዘፋ የሱፍ በወረዳው የወተት መንደር የበለጠ አስፍቶ ለመስራት ዝርያ ማሻሻልና መኖ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸው አርሶ አደሩም ባለሙያ የሚሰጣቸው ምክረ ሀሳብ በተገቢው በመጠቀም በትኩረት መስራት ይኖርባቸዋል።
አቶ ተማም በደዊና አቶ መሀመድ ከጌታ ወረዳ አታዞ ቀበሌ እንዲሁም ወይዘሮ አለምነሽ መዝገቡ ከአረቅጥ ከተማ እንዳሉት፤ በሀገረ-ሰብ ከብት በቀን 2 ሊትር ወተት የሚገኝ ሲሆን ዝርያቸው የተሻሻሉ ከብቶች በማርባት በቀን ከ4 እስከ 10 ሊትር ይገኛል።
ወይዘሮ አለምነሽ አክለውም የዝርያ ማሻሻል ስራ በተገቢው ተገንዝበው በመስራታቸው ወተት ከቤት ፍጆታቸውን ባለፈ ለገበያ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል።
የአታዞ ቀበሌ አርሶ አደሮች በበኩላቸው ከዚህ ቀደም የዝርያ ማሻሻል ስራ እድሉ እንዳላገኙ አንስተው አሁን ላይ ከብቶቻቸውን በሆርሞን ለማድራት እድል ማግኘታቸውን ጠቅሰው የዝርያ ማሻሻል ስራው በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።
ስራው ውጤታማ እንዲሆን መንግስት የመኖ አቅርቦት ውስንነት እንዲቀርፍላቸው ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፡ እንዳልካቸው ደሣለኝ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የፍትህ ሪፎርም ተግባራዊ በማድረግ በዘርፉ እየታዩ ያሉ ማነቆዎችን ማረም እንደሚገባ ተገለፀ
የመማር ማስተማር ሂደቱ የተሻለ ቢሆንም የትምህርት ግብአት እጥረት እንዳሳሰባቸው አንዳንድ ተማሪዎች ገለጹ
በከተሞች የሚስተዋሉትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ሰፊ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ