ሀዋሳ፡ ጥቅምት 12/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር እየተካሄደ ያለው መልሶ ማልማት ገፅታዋን በመቀየር ረገድ ድርሻው የጎላ በመሆኑ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚያደረጉ የከተማ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ምቹና ከሌሎች ከተሞች ጋር ተወዳደሪ እንድትሆን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አስታውቀዋል።
በሚዛን አማን ከተማ አሰተዳደር ካነጋገርናቸው ነዋሪዎች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት ከተማዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚደረገው በመልሶ ማልማት ሥራ የተለያዩ ለውጦች እየተመዘገበ መምጣቱን ገልፀዋል።
ከተማዋ ከዚህ ቀደም የነበረችበትና አሁን ያለችበት ዕድገት ጋር ስትነፃፀር በተሻለ ሁኔታ እንደምትገኝና ገፅታዋን ከመቀየሯም ባለፈ ከሌሎች ከተሞች ጋር ተወዳደሪ የሚያደርጋት በመሆኑ የበኩላቸውን ሁሉ እንደሚያደረጉም የከተማ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
በተለይም በከተማዋ የመልሶ ማልማት ሥራ ቦታ ወስደው አጥረው ያስቀመጡት ግለሰቦች በአፋጣኝ ወደልማቱ በመግባት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጡ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባ ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።
የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ቤሪ በበኩላቸው በከተማው ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ባለው ሂደት በሚዛን 52 በአማን 18 የሚሆኑ የግልና የመንግስት ቦታዎችን በመለየት ልማት ውስጥ መገባቱን ተናግረዋል።
በልማቱ ሂደት የኢንቨስትመንት ቦታዎችን የወሰዱት አካላት በውርስና በበቤተሰብ እንዲሁም ከመንግስት የተላለፉት ከይገባኛል ነፃ ባለመሆናቸውና በህግ የተያዙት ጉዳዮች ተግዳሮት የፈጠረ ቢሆንም ከእነዚህ ውጭ ሆኖ ቦታ ወስደው ያላለሙት አካላት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው እንዲሰሩ መደረጉን ዋና ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
የሚዛን አማን ከተማ በፌደራል ከተመረጡ 31 ከተሞች አንዷ ከመሆኗም ባለፈ በዩ አይ ዲ ፒ ፕሮጀክት እንድትገነባ በአፈፃፀም የተመለመለች እንደሆነ የገለፁት አቶ አሰፋ የመልሶ ማልማት ሰራን ከኮሪደር ልማት ጋር በማቀላቀልና ኮሪደር ልማት ቀርቷል የሚሉ የተዛባ አመለካከቶች ሊቀረፉ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የከተማ መልሶ ማልማት ሥራውን ውጤታማ ለማደረግ ከማህበረሰቡና ከከተማ ነዋሪዎች ጋር በመወያየት ወደተግባር መገባቱን የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ስራ ክህሎት ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊና የከንቲባው ተወካይ አቶ ምትኩ ጢሞቴዎስ ገልፀዋል።
በመልሶ ማልማትና ከተማዋን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍ ያለ መሆኑን የከንቲባው ተወካይ አውስተው በሚዛን ላይ ያለውን ልማት ከአማን ጋር አያይዞ በመስራት ለነዋሪው ምቹ ከተማን ለመፍጠር እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመቆም ልማቱን ለማፋጠን የሚያደረጉት ርብርብ የተሻለ ከመሆኑም ባለፈ የራሱን ንብረት እያነሳ ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ አቶ ምትኩ ገልፀው የኮሪደር ልማቱን ለማከናወን በጨረታ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በከተማው እየተካሄደ ያለው የመልሶ ማልማት ሥራው የክልል ተቋማት መብራት ሀይል ውሃ እና ኢትዮ-ቴሌኮም የመሳሰሉት ተቋማት ካጋጠሙት ተግዳሮቶች አንዱ መሆኑን የከንቲባው ተወካይ አስረድተው ሁሉም ለልማቱ ሊተባበር ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ፡ አብዲሳ ዮናስ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
የፍትህ ሪፎርም ተግባራዊ በማድረግ በዘርፉ እየታዩ ያሉ ማነቆዎችን ማረም እንደሚገባ ተገለፀ
የመማር ማስተማር ሂደቱ የተሻለ ቢሆንም የትምህርት ግብአት እጥረት እንዳሳሰባቸው አንዳንድ ተማሪዎች ገለጹ
በከተሞች የሚስተዋሉትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ሰፊ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ