በከተሞች የሚስተዋለውን ህገ-ወጥ አሰራር በመከላከል ፕላንን መሠረት ያደረገ ዕድገት እንዲኖር በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ
ሀዋሳ፡ ጥቅምት 11/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በከተሞች የሚስተዋለውን ህገ-ወጥ አሰራር በመከላከል ፕላንን መሠረት ያደረገ ዕድገት እንዲኖር በትኩረት መስራት እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረመስቀል ጫላ ተናገሩ።
በከተሞች የሚስተዋለውን ህገ-ወጥ ግንባታና የመሬት ወረራን ለመከላከልና ህጋዊ ስርዓት ለማስያዝ የሚያስችል ምክክር በአርባምንጭ ከተማ ተደርጓል።
የመሬት ወረራን በተደራጀ መልኩ ስርዓት በማስያዝ የከተሞችን ማዘመን እንደሚገባ ያወሱት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረመስቀል ጫላ ናቸው።
አሰራር በትክክል መሬት ላይ መውረዱን መከታተል እና የመሬት ወረራ እንዳይፈጸም ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የከተማ መስፋፋት ለአርሶ አደሩ ስጋት መሆን የለበትም ያሉት አቶ ገብረመስቀል መሬትን ከደላላው ነፃ በማውጣት ለሁለንተናዊ ለውጥ ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል።
በከተሞች የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን በማዘመን ከተሞች በገቢ ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ እንደሚገባ ገልፀው ለመንግስት ሰራተኞችም ቦታ በማዘጋጀት የቤት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በበኩላቸው በከተሞች የሚታዩ ችግሮችን መቆጣጠር አለመቻል እና ተንከባለው የመጡ ውስብስብ ችግሮችን አለመቆጣጠር ለከተሞች እድገት እንቅፋት መፍጠሩን ገልፀዋል።
የሚስተዋሉ የህግ ክፍተቶችን በአዲሱ የሊዝ አዋጅ መሰረት መፍታት ያሻል ያሉት አቶ ብርሃኑ፤ የወል መሬቶችን ከመቆጣጠር፣ ሸንሽኖ መሸጥና የመሬት አዋጅን መሰረት ያደረገ አሰራርን ከማስፈን አንፃር ችግሮች ይስተዋላሉ ብለዋል።
ችግሮችን ፈጥነን በመፍታት የከተሞችን ቅርፅ በማስተካከል የከተሞችን እድገት ለማፋጠን መስራት አለብንም ብለዋል አቶ ብርሃኑ።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የመሬት ወረራ ችግርን በመከላከል ረገድ ህገ-ወጥ ደላሎች የህግ የበላይነትን ለማስከበር ለሚደረገው ጥረት እንቅፋት መፍጠራቸውን ነው ያመላከቱት።
ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
አጀንዳዎችን በማሰባሰብ የህዝቡ ጥያቄ በተገቢው እንዲመለስ የምክክሩ ሂደቱ የላቀ አስተዋፅኦ እንዳለው ተሳታፊዎች ገለፁ
እንደሀገር ካለንበት ችግሮች ወጥተን ዜጎች ተረጋግተው የሚኖሩባት ሀገር እንድትሆን ምክክሩ እንደሚያግዝ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊ አካል ጉዳተኞች ተናገሩ
የጂንካ ዩኒቨርስቲ ለኤሶል ልዩ አዳሪ ትምህርት የተለያዩ ድጋፎችን አደረገ