የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን በልዩ ድምቀት ለማክበር ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን የክልሉ የብሔረሰቦች ምክር ቤት አስታወቀ
ሀዋሳ፡ ጥቅምት 10/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) 19ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በዓል ቀንን በልዩ ድምቀት ለማክበር ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት አስታውቋል፡፡
ምክር ቤቱ በዝግጅቱ መሪ ዕቅድ ላይ ከተዋቀረ አብይ ኮሚቴ አባላት ጋር በሚዛን አማን ከተማ ዉይይት አካሂዷል።
“ሀገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል በሃገር አቀፍ ደረጃ በአርባምንጭ ከተማ ህዳር 29/2017 ዓ.ም የሚከበረዉን 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን ምክንያት በማድረግ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሁለቱም ምክር ቤቶች በመሪ ዕቅዱ ላይ ከአብይ ኮሚቴ ጋር ዉይይት አካሂደዋል፡፡
በዉይይት መድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ መቱ አኩ፤ የበዓሉ መከበር ብዝሃነትን በማስተናገድ የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች መብት ህገ መንግስታዊ ዋስትና የተረጋገጠበት መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ መቱ አኩ በዓሉ የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ማንነታቸዉንና ባህላቸውን እንዲያስተዋውቁ ዕድል የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በሃገር አቀፍ ደረጃ ለ19ኛ ዙር የሚከበረዉ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በዓል በክልሉ ከባለፈው ዓመት ተሞክሮ በመውሰድና ጉድለቶችን በማረም በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በልዩ ድምቀት ለማክበር ታቅዶ መሰራቱን አስረድተዋል።
የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ በበኩላቸው በ18ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል አከባበር ወቅት የነበሩ ጠንካራ አፈጻጸሞችን መነሻ በመዉሰድ የዘንድሮው 19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ቀን በየደረጃዉ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ልዩ ትኩረት በመስጠት ለተፈጻሚነቱ በኃላፊነት ሊንቀሳቀሱ ይገባል ብለዋል።
በዓሉ በክልሉ በሚከበርበት ወቅት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን ይበልጥ ለማዳበር በክልሉ የሚገኙ ብሔሮችና ብሔረሰቦች በቅንጅት የሚያከብሩበትን እድል ለመጠር ከወዲሁ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የበዓሉን አከባበር በተመለከተም የተለያዩ የሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም ያልተቆራረጠ መረጃ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ከማድረግ አንጻር በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ነዉ ዋና አፈ ጉባኤዉ ያሳሰቡት።
በዉይይት መድረኩ ላይ የክልሉ ሁለቱም ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎች፣ የበዓሉ አዘጋጅ አብይ ኮሚቴ አባላት፣ የሚዲያ ተቋማትና የዞን አፈ ጉባኤዎችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸዉ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፡ ዮሐንስ አሰፋ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
የፍትህ ሪፎርም ተግባራዊ በማድረግ በዘርፉ እየታዩ ያሉ ማነቆዎችን ማረም እንደሚገባ ተገለፀ
የመማር ማስተማር ሂደቱ የተሻለ ቢሆንም የትምህርት ግብአት እጥረት እንዳሳሰባቸው አንዳንድ ተማሪዎች ገለጹ
በከተሞች የሚስተዋሉትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ሰፊ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ