የህብረተሰብን የፍትህ ጥያቄ በተገቢው ሁኔታ ለመመለስ በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን መፍታት እንደሚገባ ተጠቆመ
ሀዋሳ፡ ጥቅምት 09/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ)የህብረተሰብን የፍትህ ጥያቄ በተገቢው ሁኔታ ለመመለስ በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን መፍታት እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡
የፍትህ ሥርዓት ማነቆዎችን በማስወገድ ለተገልጋይ ህብረተሰብ ተገቢውንና ፍትሐዊ አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ የጌዴኦ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ገለፀ፡፡
የዞኑ ከፍተኛ ፍርድቤት በሥሩ ከሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች፣ ከህዝብ ክንፍና ባለድርሻ አካላት ጋር በ2016 በጀት ዓመት የእቅድ ክንውንና 2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ የሚመክር ጉባኤ በይርጋጨፌ ከተማ አካሂዷል፡፡
የጌዴኦ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ሳሙኤል በፍቃዱ በጉባኤው መክፈቻ እንደገለጹት፤ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ህብረተሰቡ ቀልጣፋ እና ፍትሐዊ አገልግሎት እንዲያገኝ በተከናወኑ ሥራዎች አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡
በአገልግሎት አሰጣጥ ወቅት የሚስተዋለውን የፍትህ ሥርዓት ማነቆዎችን በማረም ተገልጋይ ህብረተሰብ በተቋሙ ያለውን አመኔታ እንዲያሳድግና በአገልግሎት አሰጣጡ የሚያገኘውን እርካታ ለማሳደግ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ፕሬዚዳንቱ አስታውቋል፡፡
የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥን እያዛቡና ባለጉዳዮችን ለአላስፈላጊ እንግልት እየዳረጉ የሚገኙ የውስጥና የውጪ የፍትህ ደላሎች እንዳሉ የጠቆሙት አቶ ሳሙኤል እነዚህን አካላት አደብ በማስያዝ ግልጽና ተጠያቂነት የሰፈነበትን የፍትህ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድቷል፡፡
የፍትህ አገልግሎት ተደራሽነትን ከማሳደጉ ሥራ ጎን ለጎን የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደትን ለማዘመን የተጀመሩ ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ የጠቆሙት ፕረዝዳንቱ ዜጎች መሠረታዊ የህግ ግንዛቤ እንዲጨብጡ በማስተማር ብልሹ አሰራሮችን እንዲታገሉ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ክራይ ሰብሳቢነትን ጨምሮ ህብረተሰቡ በፍትህ ተቋማት ያለውን አመኔታ እንዲሸረሽር የሚያደርጉ ብልሹ አሰራሮችን ለመቅረፍ ሁሉም በጋራ ሊረባረብ ይገባል ያሉት የውይይቱ ተሳታፊዎች ህብረተሰቡም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ሳሙኤል በቀለ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ