የጤናው ዘርፍ አገልግሎት ለማጠናከር የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ሚና የላቀ መሆኑ ተገለጸ
የጤናው ዘርፍ አገልግሎት ለማጠናከር የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ሚና የላቀ መሆኑ ተገለጸ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ገለጸ።
አልቢር የልማትና ትብብር ማህበር በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቀቤና ልዩ ወረዳ ለሚገኘው አልቢር ሀሰን ኡንጃሞ ጤና ጣቢያ ከ160 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የመድህኒትና የህክምና መሳሪያዎች ድጋፍ አደረጓል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ጤና ቢሮ ምክትል ኃለፊ አቶ ሀብቴ ገብረ ሚካኤል በግግራቸው እንዳሉት የጤና አገልግሎት ያለምንም ልዩነት ለሰውልጆች በሰብዓዊነት የሚሰጥ በመሆኑ ዛሬ ለልዩ ወረዳው የተደረገው ድጋፍ ለማህበረሰቡ ጤና አጠባበቅ ትልቅ አበርክቶ መሆኑን ገልፀዋል።
እንደ ክልል በዘርፉ የሚገጥሙ የህክምና መሳርያ ግብዓቶችና የመድሃኒት አቅርቦች እጥረቶች ለመቅረፍ ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ባሻገር ማህበረሰቡን በማስተባበር ትልቅ ስራ እየተሰራ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
የተደረገው ትልቅ ድጋፍ በጥንቃቄ እና በኃላፊነት በመጠቀም ማህበረሰቡን ማገልገል እንደሚገባ ያሳሰቡት ኃላፊው በቀጠይም ከልዩ ወረዳው ጋር በመቀናጀት የጤናው ዘርፍ ለማጠናከር እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኤዶሳ በበኩላቸው የአልቢር ልማት ማህበር ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በልዩ ወረዳው በጤና፣ በትምህርት፣ በበጎ ፈቃድና በተለያዩ ሰው ተኮር ስራዎች በርካታ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
ልማት ማህበሩ አስተባብሮ ለአልቢር ሀሰን ኡንጀሞ ጤና ጣቢያ ላደረገው የ160 ሚሊዮን ብር የመድሃኒት እና የህክምና መሳሪያ ድጋፍ በወረዳው ህዝብና መንግሥት ስም አመስግነዋል።
የአልቢር ልማትና ትብብር ማህበር የበላይ ጠባቂ የሆኑት የክብር ዶክተር ሼህ ሱልጣን አማን ልማት ማህበሩ ከተመሠረተ 20 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በሀገራችን በሚገኙ በአምስት ክልሎችና ሁለት የከተማ መስተዳደሮች ውስጥ የልማትና ሰብአዊ ድጋፎችን የሚያደርግ ሀገር በቀል ድርጅት መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በጤናው ዘርፍ፣ በንፁህ መጠጥ ውሃ፣ በእናቶችና ህፃናት፣ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታዎችና ሌሎችም ሰው ተኮር ድጋፎችን የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።
የአልቢር ልማትና ትብብር ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ያሲን አረቦ ግብረሰናይ ድርጅቱ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባሻገር በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ወቅታዊና ዘለቄታዊ ድጋፍ በመስጠት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት እያሻሻለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ማህበሩ ለልዩ ወረዳው የሚያደርገው ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀው የተደረገው የመድሃኒትና የህክምና መሳሪያ ድጋፍ በአግባቡ አገልግሎት ላይ ማዋል እንደሚገባ አሳስበዋል።
በርክክብ መርሐግብሩ ላይ አግኝተን ያነጋገርናቸው የልዩ ወረዳው ነዋሪዎች አቶ አብደላ በሽራ እና ወ/ሮ ሽታዬ አወል ቡሹራ በሰጡት አስተያየት ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ለልዩ ወረዳው ባበረከተው የመድሃኒት እና የህክምና መሳሪያ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
የተገኘው ድጋፍ በዘርፉ ይስተዋል የነበረው የመድሃኒት እና የህክምና መሳሪያ እጥረት የሚቀርፉ በመሆኑ በአግባቡ አገልግሎት ላይ ማዋል እንደሚገባ ተናግረዋል።
በርክክብ ስነስርዓቱ ጠንካራ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ሽልማትና እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
ዘጋቢ፡ አዱኛ ትዕዛዙ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የሲዳማ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት 9ኛ መደበኛ ጉባኤ #ደሬቴድ፣ ሐምሌ 07/2017 ዓ.ም
የኮሪደር ልማት ሥራዎች የሕብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ እየቀየረ መምጣቱን ነዋሪዎች ተናገሩ
የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተከናወኑ ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ መሰረተ ልማትና የመንግስት ሀብት ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስገነዘበ