አሁን ላይ  እየተባባሰ የመጣውን የወባ በሽታ ስርጭት ለመቆጣጠር በተቀናጀ ሁኔታ  እየተሠራ ነው –  በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት

አሁን ላይ  እየተባባሰ የመጣውን የወባ በሽታ ስርጭት ለመቆጣጠር በተቀናጀ ሁኔታ  እየተሠራ ነው –  በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 09/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) አሁን ላይ  እየተባባሰ የመጣውን የወባ በሽታ ስርጭት ለመቆጣጠር በተቀናጀ ሁኔታ  እየተሠራ መሆኑን  በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ገለፀ።

በተፈጠረላቸው ግንዛቤ መሠረት በሽታውን ለመከላከል ቢጥሩም በአንዳንድ አካባቢ የስርጭቱ መጠን ያለ መቀነስ ችግር መኖሩን አንዳንድ የልዩ ወረዳው ነዋሪዎች ተናገሩ።

በጠምባሮ ልዩ ወረዳ የዋሮ፣ የጋዕቻና  የቀለጣ  ዙሪያ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት የጤና ባለሙያዎች በተፈጠረላቸው ግንዛቤ የወባ በሽታን ለመከላከል የሚጠበቅባቸውን በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በቀበሌያቸው  በሀምሌ ወር ቤት ለቤት የኬሚካል ርጭት መከናወኑንና ባለሙያዎችም ወርደው ድገፍ  እያደረጉ መሆናቸውን የጠቆሙት አስተያየት ሰጭዎቹ በአንዳንድ አካባቢዎች ግን ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት የስርጭቱ መጠን እየጨመረ መጥቷል።

መንግስት  አልፎ አልፎ ለሚስተዋለው የመድኃኒት እጥረትና በህብረተሰቡ አቅም ለማፋሰስ በማይቻሉ በተለያዩ ምክንያት ለተጠራቀሙ ወሃዎች መፍትሔ እንዲያበጅለትም  ጠይቀዋል።

ከጋዕቻ ጤና ጠቢያ ወደ ዋሮ ቀበሌ በመሄድ ለወባ ትንኝ መራቢያ ምክንያት ሊሆኑ በሚችሉ በታቆሩ፣ ጨፌ በሆኑና በተጠራቀሙ ውሃዎች ላይ የኬሚካል ርጭት ሥራ ሲሠሩ  አግኝተን ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች  አቶ አበራ አበበ እና ቦጋለ ቦቃ የወባ በሽታን ስርጭት መቆጣጠር እንዲቻል ኃላፊነታቸውን በተገቢው በመወጣት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ም/ኃላፊና በሽታ የመከላከልና ጤና የማጎልበት ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አማረ በየነ እንደተናገሩት በልዩ ወረዳው የወባ በሽታን መከላከል እንዲቻል ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች በተቀናጀ ሁኔታ እየተከናወኑ ይገኛል።

በዚህም ከሦሱቱም ጤና ጠቢያዎችና ከሙዱላ የመጀመሪያ ደረጀ ሆስፒታል ለእያንዳንዱ ቀበሌ  ከጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በጋራ በመሆን ህዝቡን የሚደግፉ ሁለት ሁለት በለሙያዎች ተመድበው በየቦተው በተጠራቀሙ ውኃዎች ላይ “አብዮት  ኬሚካል”የተሰኘ ኬሚካልን በ43 ትላልቅ ማቆሪያዎች ደግሞ “አኳትን”በመጨመር የመከላከል ሥራው ትኩረት ተሰጥቶበት እየተሠራ መሆኑንም አቶ አማረ  ተናግረዋል።

የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ሀላፊ ዶ/ር ፀጋዬ ሸሜቦ በበኩላቸው እየጨመረ የመጣውን የወባ በሽታ ስርጭት ለመከላከል  ከፍተኛ ጥልቀት በላቸው ቦታዎች በተጠራቀሙ  ውኃዎች ላይ በየወሩ ኬሚካል በመርጨት  በሰው አቅም የማይቻሉትን ደግሞ  በማሺኔሪዎች በመታገዝ ማፋሰስ ወይም ማዳፈን እንዲቻል የመንገድ ሥራ ከሚሰሩ አካላት በመነጋገር ለመቅረፍ  እየሠራን ነው ብለዋል።

የወባ በሽታ ስርጭቱን ለመቆጣጠር ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ ስርጭቱን መቀነስ አልተቻለም ያሉት ዶ/ር ፀጋዬ ህብረተሰቡ የአልጋ አጎበርን አጠቃቀም  በማስተካከልና የመከላከያ ዘዴዎቹን በጤና ባለሙያዎች በተፈጠረው ግንዛቤ መሠረት በመተግበር የወባ በሽታን መከላከል እንዲችል መልዕት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፡ ሙሉነሽ ለማ – ከሆሳዕና ጣቢያችን