በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የዳራሮ ሁለተኛ ደረጃ የሽግግር አዳሪ ትምህርት ቤት ተመረቀ
ሀዋሳ፡ ጥቅምት 09/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የዳራሮ ሁለተኛ ደረጃ የሽግግር አዳሪ ትምህርት ቤት ተመርቋል።
በብሔሩ የዘመን መለወጫ በዓል ዳራሮ የተሰየመው ትምህርት ቤቱ፣ በጌዴኦ ዞን አስተዳደር እና ጌዴኦ ልማት ማህበር ትብብር የተገነባ መሆኑ ተገልጿል።
የዳራሮ ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤትን መርቀው የከፈቱት የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ(ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ እንደሀገር የደረሰውን የትምህርት ስብራትን ማውራት ብቻ ሳይሆን ለመፍታት ተግባር ያስፈልጋል።
የሽግግር አዳሪ ትምህርት ቤቱ በዞኑ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን ለሚገነባው ትምህርት ቤት መነሻ የሚሆን ነው ብለዋል አስተዳዳሪው።
በትምህርታቸው ጠንካራ ሆነው ነገር ግን በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጡ መመዘኛዎችን ማለፍ ያልቻሉ ተማሪዎች በመኖራቸው፣ እንደነዚህ ያሉ ትምህርት ቤቶች ውጤታማ እንዲሆኑ የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል።
በግንባታ ሂደቱ ተሳታፊ ሆነው አስተዋጽኦ ያበረከቱ ባለድርሻ አካላት እና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን አስተዳዳሪው አመስግነዋል።
የልማት ማህበሩ ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ እጩ ዶክተር ታጠቅ ዶሪ፣ የጌዴኦ ልማት ማህበር ለረጂም ዓመታት ትምህርትን ጨምሮ ሌሎች ለህዝቡ የሚሆኑ በርካታ የልማት ሥራዎችን እየሠራ ነው ብለው፣ የተገነባው የአዳሪ ትምህርት ቤት የአካባቢውን ኢኮኖሚ በሰው ሀብት ለመገንባት አስተዋጽኦ ያበረክታል ነው ያሉት።
የዳራሮ አዳሪ ትምህርት ቤት የትምህርት ስብራትን ለመጠገን የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ መሆኑ ተገልጿል።
የዳራሮ አዳሪ ትምህርት ቤት፣ በጌዴኦ ልማት ማህበር በቀድሞ ሆስቴል ማዕከል ላይ የተገነባ ሲሆን የመማሪያ፣ የቤተ ሙከራ ክፍሎች፣ የመመገቢያ አዳራሽ እና አጥር ግንባታና ጥገና ተከናውኖ የመማር ማስተማሩን ሥራ ጀምሯል።
በምረቃ ስነስርዓቱ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ዝናቡ ወልዴን ጨምሮ የዞን፣ ከተማና የወረዳ የሥራ ሃላፊዎች ፣ አባገዳዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች ታድመዋል።
በመርሀ ግብሩ የታደሙ ተሳታፊዎች ለአዳሪው ትምህርት አሻራቸውን ለማሳረፍ የገንዘብ ድጋፍ አበርክተዋል።
ዘጋቢ: እስራኤል ቅጣው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ