ሀዋሳ፡ ጥቅምት 09/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በኮቾሬ ወረዳ በተለያዩ ምክንያቶች በመበላሸት ለረጅም ዓመታት የተቋረጡ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተጠግነው ለሕብረተሰቡ ግልጋሎት ክፍት ተደርገዋል።
መርሐግብሩን በንግግር የከፈቱት የኮቾሬ ወረዳ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ ባለፉት ጊዜያት በወረዳው ተገንብተው ለሕብረተሰቡ ይሰጡ የነበሩ የቆዩ የራኮ፣ ሲሶታና ሲግጋ ቀበሌ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በመበላሸታቸው ለከፍተኛ የውሃ እጥረትና ቅሬታ ፈጥረው እንደነበረ አስገንዝበዋል።
በአሁኑ ሰዓት ወረዳው ከዞን መንግስትና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ክፍሎች ጋር በመቀናጀት ባደረገው ብርቱ ጥረት ፕሮጀክቶቹ 85 በመቶ ተጠግነው ለሕብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ገልፀው ቀሪውንም ሥራ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ በጀት መድበው ያላሰለሰ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን አሰረድተዋል።
አቶ ዘገዬ ብርሃኑ የኮቾሬ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ኃላፊና የብልግና ፓርቲ ጽ/ቤት ተወካይ ናቸው።
የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ከመሠረታዊ የሰው ልጆች ፍላጎቶች መካከል የመጀመርያው መሆኑን በመግለፅ በወረዳው አልፎ አልፎ በሚስተዋለው የበጀት እጥረትና የሰው ኃይል ማነስ ምክንያት ንጹህ የመጠጥ ውሃ እጦት እንደሚከሰት ተናግረዋል።
አክለውም ህብረተሰቡም መንግስት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ያፈሰሰባቸውን ፕሮጀክቶች በአግባቡ በመገልገል ለጉዳትና ለልዩ ልዩ ብልሽቶች እንዳይዳረጉ መንከባከብ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
የጌዴኦ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊና የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ አበባየሁ ኢሳያስ በበኩላቸው በአካባቢው ለረዥም ጊዜያት በሕብረተሰብ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ ፈጥሮ የቆየው ይህ ፕሮጀክት የዞኑ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ባደረገው ያልተቆጠበ ጥረት ለአገልግሎት በመብቃቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ለሕዝብ የተገባውን ቃል በተግባር በማሳየት የብልጽግና ጉዟችንን እናስቀጥላለን ያሉት አቶ አበባየሁ፣ ሕብረተሰቡ ዳግም ለውሃ እጥረት እንዳይዳረግ ፓርቲው በፖለቲካ አመራር ጉዳዩን በቅርበት በመከታተል የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ ነው ያብራሩት።
ዕጩ ዶክተር ዳዊት ጀቦ የጌዴኦ ዞን ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ ሲሆኑ መምሪያው ሕብረተሰቡ በንጹህ የመጠጥ ውሃ ዙሪያ የሚያነሳቸው ጥያቄዎችን ለመመለስ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመግባባት ወደ ተግባር መግባቱን አስታውቀዋል።
በቀጣይም ተመርቀው ለሕዝብ አገልግሎ የሚውሉ በርካታ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን የተናገሩት ኃላፊው የራኮ፣ ሲሶታና ሲግጋ የውሃ ፕሮጀክቶች ከአካባቢው አልፈው ለኦሮሚያ ክልል አጎራባች ቀበሌዎች ተደራሽ መሆን እንደሚችሉ አስረድተዋል።
በዞኑ አጠቃላይ የንጹሕ መጠጥ ውሃ ሽፋን 26 በመቶ ብቻ መሆኑን ጠቁመው መምሪያው በ2017 ዓ.ም በሁሉም ወረዳዎች ሽፋኑን ለማሳደግ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ ከዞን፣ ከክልልና ከፌዴራል መንግሥት ጋር ተናብበው እየሠሩ እንደሚገኝም አክለዋል።
አቶ ከፍያለው አበበና ወይዘሮ ማርታ ወርቁ በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል በአካባቢያቸው ተገንብተው የነበሩ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በደረሰባቸው ብልሽት በመጎዳታቸው ለዘርፈ ብዙ ችግሮች ተዳርገው መቆየታቸውን ጠቁመው በአሁኑ ሰዓት ተሠርተው ለአገልግሎት በመብቃታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ እስራኤል ብርሃኑ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ