የቁጠባ ባህል በማዳበራቸው ጥሪት ማፍራትና ኑሮአቸውን ማሻሻል መቻላቸውን በደቡብ ኦሞ ዞን የኛንጋቶም ወረዳ አርብቶ አደሮች ተናገሩ

የኦሞ ባንክ ኛንጋቶም ቅርንጫፍ በበኩሉ ካለፈው አመት ወዲህ ከ10 ሺህ በላይ የቁጠባ ደንበኞች በማፍራት ከ15 ሚሊየን ብር በላይ ማስቆጠብ መቻሉን ገልጿል።

ከተቋሙ ደንበኞች መካከል የሊበሬና ሎሬንካቻዎ ቀበሌ ነዋሪ አርብቶ አደር ሶያ ኤጉዋም፣ ኤርምያስ ሎግቸሬ እና ወ/ሮ ናቱኮይ ባይሌ እንደገለጹት በተሰጣቸው ግንዛቤ ተነስተው በግልና በማህበር መቆጠብ ከጀመሩ አስር አመታትን አሳልፈዋል።

በቆይታቸውም ከመቶ ሺህ ብር በላይ የሚገመት ካፒታል ማስመዝገብ፣ ከብቶችና ሞተር ብስክሌት መግዛት፣ ቤት መስራትና ኑሯቸውን ማሻሻል መቻላቸውን ጠቁመው፤ ተቋሙ ውስጥ ቁጠባቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉና ገንዘብ ለሚያባክኑ አካላትም አርአያነታቸውን እንዲከተሉ መክረዋል።

የኦሞ ባንክ ኛንጋቶም ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ዳግማዊ መኮንን እንደገለጹት፤ በወረዳው የሚገኘውን አርብቶ አደር ማህበረሰብ የቁጠባ ባህል ለማዳበር ባለፉት አመታት የተሰራው የተቀናጀ ተግባር ውጤት አስገኝቷል ብለዋል።

ከ2016 በጀት አመት ጀምሮም በተቋሙ ከ10 ሺህ 4 መቶ በላይ የቁጠባ ደንበኞችን በማፍራት ከ15 ሚሊየን ብር በላይ ማስቆጠብ መቻሉን አስረድተዋል።

በ2017 የመጀመሪያው ሩብ አመትም አርባ አምስት አዲስ የቁጠባ ደንበኞች በማፍራት ከ2 መቶ 65 ሺህ ብር በላይ ማስቆጠብ መቻሉንና የሕብረተሰቡ የቁጠባ ባሕል ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መምጣቱን ስራ ስክያጁ አመላክተዋል።

ዘጋቢ፡ ተመስገን ሰይፉ – ከጂንካ ጣቢያችን