የልብ ህመም አጋጥሞት የነበረው ኑሳይር ማዝራዊ ወደ ልምምድ መመለሱ ተገለፀ

ከልብ ጋር የተያያዘ ህመም አጋጥሞት የነበረው የማንቸስተር ዩናይትዱ የመስመር ተከላካይ ኑሳይር ማዝራዊ ወደ ልምምድ መመለሱ ተገልጿል።

ሞሮኮአዊው ተጫዋች ባጋጠመው ህመም አነስተኛ የቀዶ ህክምና አድርጎ ነበር።

አሁን ላይ ግን ማዝራዊ ከህመሙ በማገገሙ ማንቸስተር ዩናይትድ በነገው ዕለት ከብሬንትፎርድ ጋር ከቀኑ 11 ሰዓት ለሚያከናውነው የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታ በስብስቡ እንደሚካተት አሰልጣኝ ኤሪክ ቴንሃግ አሳውቀዋል።

በሌላ በኩል የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል ወሳኝ ተጫዋቾቹ ቡካዮ ሳካ፣ ካይ ሃቨርትዝ እና ቶማስ ፓርቴ ለጨዋታ ዝግጁ መሆናቸው ተገልጿል።

 የክለቡ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ እንደገለፁት ሶስቱም ተጫዋቾች ከጉዳታቸው አገግመው በነገው ዕለት ከበርንማውዝ ጋር በሚካሄደው የሊጉ መርሐግብር መሰለፍ እንደሚችሉ ገልፀዋል።

ስፔናዊው አሰልጣኝ አያይዘውም የክለቡ አንበል ማርቲን ኦዴጋርድ በህዳር ወር ከሚካሄደው የሀገራት ጨዋታ አስቀድሞ ወደ ጨዋታ እንደሚመለስ አመላክተዋል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ