ሀዋሳ፡ ጥቅምት 08/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሰለጠነ የሰው ሀይል በማፍራት የማህበረሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመፍታት በሚደረገው ርብርብ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ የቡሌ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ አስታወቀ፡፡
በኮሌጁ በንድፍና በተግባር የሚሰጠው ስልጠና ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል እንደሆነም ተማሪዎች ገልጸዋል።
የቡሌ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጌዴኦ ዞን ከሚገኙ ኮሌጆች አንዱ ሲሆን የሰለጠነ የሰው ሀይል በማፍራት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ የሚገኝ ተቋም መሆኑን የኮሌጁ ዋና ዲን አቶ ዘመን ዳንኤል ተናግረዋል።
የመማር ማስተማር ሥራ ለማስጀመር የትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት በየደረጃው የሚያስተምሩ መምህራንን፣ በቂ የመማሪያ ክፍሎችን፣ ቤተ ሙከራና የመሳሉትን በሟሟላት ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት በማጠናቀቅ ምዝገባ ለመጀመር፣ ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሚያስቀምጠውን የመቁረጫ ነጥብ እየተጠባበቁ መሆናቸውን ዲኑ ተናግረዋል፡፡
የኮሌጁ ምክትል ዲንና የሥልጠና ተቋማት አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደረጀ ጀቦ፤ ተወዳደሪና ብቁ በዕውቀት የተገነቡ ተማሪዎችን በማፍራት ለማህበረሰቡ በቂ አገልግሎትን የሚሰጥ ዜጋ ለማፍራት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀው የአቅም ማነስ ላለባቸውም ልዩ ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ኮሌጁ ሥራ ከጀመረበት ከ2012 ዓ.ም ከሚመለከታቸው አካላት በመቀናጀት የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ መሠረት ያደረጉ የትምህርት መስኮችን በመክፈት እያሰለጠ እንደሚገኝ ተናግረው በማኑፋክቸሪንግ፣ በእንስሳት እርባታ፣ በአውቶሞቲቭ ቴክኖሎጂ፣ በአይሲቲ፣ በኮንስትራክሽንና በመሳሰሉት በ2017 ትምህርት ዘመን 6 መቶ ተማሪዎችን ተቀበሎ ለማስተማር መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
የኮሌጁ ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ ያገኙትን በተግባር ተደግፎ በመማር ውጤታማ እንዲሆኑ እየሰራ እንደሚገኝና ሠልጣኞች ከቴክኖሎጂ ጋር ራሳቸውን በማስተሳሰር የራሳቸውንና የማህበረሰቡን ችግር የመፍታት አቅም እንዲያጎለብቱ እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኮሌጁ ምክትል ዲንና የቴክኖሎጂ ሽግግርና ኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍና ክትትል ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፈቃዱ ፌይሳ ናቸው።
መምህር ሀብታሙ ጠቀሰ እና ሠላሙ ሽጉጤ በኮሌጁ የአይሲቲና የኤሌክትሪካል እንስታሌሽን አሰጣልኞች ሲሆኑ ተማሪዎችን በዕውቀትና በክህሎት ብቁ እንዲሆኑ ተግባርን መርህ ያደረገ ትምህርት በመስጠት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አሰልጣኞቹ አክለውም ከኮሌጁም ሆነ ከሚመለከታቸው አካላት የሚደረግላቸው ቁሳዊና ሥነ ልቦናዊ ድጋፍና ክትትል አበረታች መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም ወደ ኮሌጁ የሚቀላቀሉ ተማሪዎችን በዕውቀትና በክህሎት ብቁ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል።
ካነጋገርናቸው ተማሪዎች መካከል ተማሪ ወንጌላዊት ዋቃየሁ እና ፀጋዬ በየነ በሰጡት አስተያየት በኮሌጁ ከሚያገኙት ዕውቀት በተጨማሪ ወደማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ ሙያዊ ስነ ምግባራቸውን ጠብቀው ማገልገል የሚያስችላቸውን ግንዛቤ እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም ወደ ኮሌጁ ለሚመጡ አዳዲስ ተማሪዎች በኮሌጁ ቆይታቸው የቀሰሙትን ዕውቀትና ተሞክሮ በማጋራት አቀባበል እንደሚያደርጉም ተማሪዎቹ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ ዘርሁን ሹፌር – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ