የኦሞ ሰው ሰራሽ ሀይቅ ቱሪስት በመሳብ እና ለከተማው ተጨማሪ ውበት በመሆን የበሌ አዋሳ ከተማ እድገት እንዲፋጠን አድርጓል – ነዋሪዎቹ

የኦሞ ሰው ሰራሽ ሀይቅ ቱሪስት በመሳብ እና ለከተማው ተጨማሪ ውበት በመሆን የበሌ አዋሳ ከተማ እድገት እንዲፋጠን አድርጓል – ነዋሪዎቹ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 08/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኦሞ ሰው ሰራሽ ሀይቅ ቱሪስት በመሳብ እና ለከተማው ተጨማሪ ውበት በመሆን በወላይታ ዞን የበሌ አዋሳ ከተማ እድገት እንዲፋጠን ማድረጉን ነዋሪዎቹ ገለጹ፡፡

ከተማዋን ከሌሎች ካደጉት ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ ለማድረግ አቅዶ እየሰራ መሆኑን የበሌ አዋሳ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል።

የበሌ አዋሳ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ አሸናፊ ኤሊያስ እና ወ/ሮ አሥራት ዘዉደ በሰጡት አስተያየት በከተማዋ በርካታ መሰረተ ልማቶች እየተሰሩ እንደሚገኙና የመንገድ መሰረተ ልማት አካል የሆነው የሶዶ ታርጫ አስፓልት መንገድ ለከተማዋ ዕድገት ትልቁን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል።

ከተማዋን ለኑሮ ተመራጭ እና ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ እየተሰራ ያለው የአረንጓዴ አሻራ ሥራ የበሌ አዋሳ ከተማ ዕድገት በዉበት እንዲደገፍ ማድረጉን ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ ሻለቃ ኡኩሞ ጃፎ ተናግረዋል።

በተጨማሪም የኦሞ ሰው ሰራሽ ሀይቅ ቱሪስት በመሳብ እና ለከተማው ተጨማሪ ውበት በመሆን የበሌ አዋሳ ከተማ እድገት እንዲፋጠን ማድረጉንም ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል።

ከመሠረተ ልማቶች መካከል የግልና የመንግስት ጤና ተቋማት፣ መንገድ፣ ዉሃ፣ መብራት፣ ማደያዎችና ሆቴሎች ተገንብተው ለከተማዋ ማሕበረሰብ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውም ገልጸዋል።

በበሌ አዋሳ ከተማ የሚታየው ዕድገት የሕብረተሰብ እና የከተማ አስተዳደር ቅንጅታዊ ሥራ ዉጤት መሆኑን የበሌ አዋሳ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታምሩ ታንጋ ጠቁመዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት አዳዲስ መሰረተ ልማቶችን ለመስራት መታቀዱን የገለፁት ኃላፊው፤ የከተማ ውሰጥ ለውሰጥ መንገዶች ኮብልስቶን ሥራ እና ዲች ቀዳሚዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሌ አዋሳ ከተማን ከሌሎች አጎራባች ከተሞች ጋር በዕድገት ተወዳዳሪ ለማድረግ የተለያዩ ስትራቴጂዎች ተቀርፀው እየተሠሩ መሆናቸውን የበሌ አዋሳ ከተማ አሰተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ ዘመኑ በላይነህ ተናግረዋል።

የበሌ አዋሳ ከተማ የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት መዳረሻ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ በከተማዋ ኢንቨስት ለማድረግ ለሚፈልጉ አካላት የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አቶ ዘመኑ አስታውቀዋል።

ዘጋቢ፡ ሰላሙ ማሴቦ – ከዋካ ጣቢያችን