በተለያየ ዘርፍ በማህበር በመደራጀት ተጠቃሚ መሆናቸውን በሐመር ወረዳ በማህበር የተደራጁ ወጣቶች ተናገሩ

በተለያየ ዘርፍ በማህበር በመደራጀት ተጠቃሚ መሆናቸውን በሐመር ወረዳ በማህበር የተደራጁ ወጣቶች ተናገሩ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 07/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በተለያየ ዘርፍ በማህበር በመደራጀት ተጠቃሚ መሆናቸውን በደቡብ ኦሞ ዞን በሐመር ወረዳ በዲመካ ከተማ ስር በማህበር የተደራጁ ወጣቶች ተናግረዋል።

በሐመር ወረዳ በማህበር ተደራጅተው ከሚንቀሳቀሱት መካከል የፍራፍሬና አትክልት አቅራቢ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ተስፋነሽ ዛዴ፣ ፀጋዬ እና ቤተሰቦቹ የሸቀጣሸቀጥ አቅራቢ ማህበር ፀሃፊ ወጣት ምስገኑ ገለታ በጋራ እንደገለፁት፤ ከዚህ ቀደም ሥራ አጥ በነበሩ ጊዜ በኢኮኖሚ ይቸገሩ እንደነበረ ገልፀው አሁን ላይ መንግስት ባመቻቸላቸው የሥራ ዕድል ፈጠራ መሠረት በማህበር በመደራጀት ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡

አሁን ላይ ከነበረባቸው የኢኮኖሚ ጫና ተላቀው እራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን በማስተዳደር ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አክለውም እያንዳንዳቸው በ5ሺህ ብር እና በ35ሺህ ብር መነሻ ወደ ሥራ በመግባት አሁን ላይ ከ20 ሺህ ብር እና ከ3 መቶ ሺህ ብር በላይ ካፒታል እንዳላቸው ገልፀው በቀጣይ በተሻለ ዘርፍ ለመንቀሳቀስ መንግስት የሼድ ግንባታ እንዲያመቻችላቸው ጠይቀዋል።

የሐመር ወረዳ ኢንተርፕራይዝና ሥራ ዕድል ፈጠራ ልማት ጽ/ቤት የወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንስፔክሽን ባለሙያ የሆኑት አቶ ተሣነው ታዬ በበኩላቸው በወረዳው በቅድሚያ የሥራ አጦችን ፍላጎት በማስቀደም ሥራ አጡ ወጣት በመረጠው ዘርፍ በማሰማራት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ እየተደራጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በተጨማሪም ማህበራቱ በቆጠቡት መጠን ብድር በማመቻቸት በከተማ ግብር፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በንግድና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ 27 ማህበራትን በማደራጀት ሙያዊ ድጋፍና ክትትል እያደረጉ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

የሐመር ወረዳ ኢንተርፕራይዝና ሥራ ዕድል ፈጠራ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አርሻል ስላል እንደገለፁት፤ እንደ ተቋሙ በገጠርና በከተማ ውስጥ ሥራ አጥ ወጣቶችን በመለየትና አደራጅቶ ወደ ሥራ ከማስገባት አኳያ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ተሰርተዋል።

በዚህም መሠረት በአጋር ድርጅቶች ድጋፍ በገጠር 67 ማህበራት በማድለብ እና በማሞከት የተደራጁ ሲሆኑ በከተማ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና ግንባታ ዘርፍ 27 ማህበራት መኖራቸውን ገልፀዋል።

በወረዳው በአጠቃላይ 94 ማህበራት በሥራ ላይ መሆናቸውን በመግለፅ ለማህበራቱ አስፈላጊውን የሼድ ግንባታ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘጋቢ: አርኝሮ አርሻል – ከጂንካ ጣቢያችን