የጎፋ ዞን ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ በዞኑ ለሚገኙ 50 አካል ጉዳተኞች 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የሚገመት የዊልቸር ድጋፍ አደረገ
ድጋፉ በአጋፔ ሞቢሊቲ ኢትዮጵያ አማካኝነት ከ”ፍሪ ዊልቸር ሚሽን” ከሚባል የውጪ ሐገር ግብረ ሰናይ ድርጅት በነፃ የተበረከተ መሆኑም ተገልጿል።
በጎፋ ዊልቸር የሚያስፈልጋቸው 2 መቶ 20 አካል ጉዳተኞች ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት ለ52ቱ ድጋፍ ተደርጓል።
አሁን ደግሞ 50 የአካል ጉዳተኞች የዊልቸር ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት የዞኑ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ አቶ ተመስገን ጌታቸው፤ ቀሪ 1 መቶ 18 ውልቸር ፈላጊ አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ መምሪያው ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ በርክብክቡ ሥርዓት ላይ ገልጸዋል።
በፕሮግራሙ የተገኙት የጎፋ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ታደለ ያዕቆብ የብልጽግና ፓርቲና መንግስት ከምንም በላይ ለሰው ልጆች ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሰራ አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የዞኑ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት አካል ጉዳተኞች ድጋፍ እንዲያገኙ እያደረገ ስላለው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
የአጋፔ ሞቢሊቲ ኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሚኪ ዘላለም በበኩላቸው አጋፔ ሞቢሊቲ ኢትዮጵያ “መሬት የመንፏቀቅ ዘመን ያበቃል” የሚል ዓላማ አድርጎ የሚሰራ ድርጅት መሆኑን ገልጸዋል።
ድርጅቱ እሰካሁን በሀገሪቱ በተለያዩ ክልሎች ከ4000 በላይ ለሚሆኑ አካል ጉዳተኞች የዊልቸር ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዝዳንት አቶ ሙሴ ጉማራ፤ አካል ጉዳተኝነት እንደ ጥላ የሚከተለን ክስተት ስለሆነ ደግሞም መቼ አካል ጉዳተኛ እንደምንሆን ስለማናውቅ ሁላችንም አካባቢያችንን ለራሳችን ብለን ምቹ ልናደርግ ይገባል ብለዋል።
ድጋፍ የተደረገላቸው አካል ጉዳተኞች እና አሳዳጊ ወላጆች በሰጡት አስተያየት በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን ገልጸው፤ ለተደረገላቸው ድጋፍም ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ዘጋቢ: አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ