በጋሞ ዞን ከ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የትራኮማ በሽታ መከላከያ መድሀኒት እደላ ተደረገላቸው – የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ
በጋሞ ዞን ከ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የትራኮማ በሽታ መከላከያ መድሀኒት እደላ እንደተደረገላቸው የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ።
በዞኑ 15 መዋቅሮች ከፍተኛ የሆነ የትራኮማ ስርጭት እንደሚስተዋልም ተጠቅሷል።
የትራኮማ በሽታ አይነስውርነትን ከሚያስከትሉ የአይን በሽታዎች ውስጥ የሚጠቀስ ሲሆን የግልና የአካባቢን ንጽህና ባለመጠበቅ የሚከሰት በሽታ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በዚህ ረገድ ያነጋገርናቸው የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ በሽታ መከላከልና ጤና ማበልጸግ ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ ቻለው ንጋቱ የትራኮማ በሽታን መከላከል እንዲያስችል በዞን ደረጃ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እና የመድሀኒት እደላ ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል።
በዞኑ በየአመቱ የዳሰሳ ጥናት እንደሚደረግና ባለፈው አመት በዞኑ 15 መዋቅሮች ከፍተኛ የሆነ የትራኮማ ስርጭት እንዳለባቸው የዳሰሳ ጥናቱ የሚሳይ በመሆኑ በየጊዜው የመድሀኒት እደላ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
በዞኑ የቦንኬ፣ ገረሴ ከተማና ገረሴ ዙሪያ፣ ደራማሎ ወረዳና፣ የአርባምንጭ ከተማ ከመድሀኒት እደላ ነጻ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለረዥም አመታት የበሽታው ስርጭት በስፋት ከሚታይባቸው ወረዳዎች ውስጥ በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ 14 ዙር የመድሀኒት እደላ የተደረገ ሲሆን ከመድሀኒቱ ባሻገር የግልና የአካባቢ ንጽህና መጠበቅ አስፈላጊ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የበሽታው ስርጭት በስፋት መኖሩ በተለየባቸው 15 መዋቅሮች ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የመድሀኒት እደላው ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል አቶ ቻለው።
ቁሳቁስን ጨምሮ የዘመቻውን ሙሉ ወጪ በመሸፈን ረገድ ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ደራሼ፣ አሌ፣ ባስኬቶና ዳውሮ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ያበረከተው አስተዋጽኦ የሚደነቅ ነው ብለዋል።
የትራኮማ በሽታ የውሀ እጥረት፣ የንጽህናና የቆሻሻ አወጋገድ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች በስፋት የሚታይ በመሆኑ ህብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባው ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ