ወጣቶችን በማደራጀትና በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ በማሠማራት በመልካም ስብዕና ማነፅ እንደሚገባ ተገለጸ

ወጣቶችን በማደራጀትና በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ በማሠማራት በመልካም ስብዕና ማነፅ እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 06/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ወጣቶችን በማደራጀትና በማሠማራት በሥራ ባህልና በመልካም ስብዕና ማነፅ እንደሚገባ የኣሪ ዞን ሽግግር ምክር ቤት አስታወቀ።

በዞኑ ደቡብ ኣሪ ወረዳ በግብርናዉ ዘርፍ የተደራጁ ወጣቶች ማህበራት ዉጤታማ መሆናቸውም ተመላክቷል።

የኣሪ ዞን ሽግግር ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ወ/ሮ ስመኝ ተስፋዬ እንደገለፁት የወጣቶች የሥራ ባህል ለማጎልበትና በመልካም ስብዕና ከማነፅ አኳያ ቀጣይነት ያለው ሥራ ማከናወን ይገባል።

በደቡብ ኣሪ ወረዳ በግብርና ስራ መስክ የተሰማሩ ወጣቶች ማህበራት በሚደረግላቸው ድጋፍ በአጭር ጊዜ የተሻለ ዉጤት ማስመዝገብ መቻላቸውን ገልጸዋል።

ለደንና ለምግብነት የሚያገለግሉ ችግኞችን በማዘጋጀት ለአካባቢው አርሶአደሮች በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ሥራ የተደራጁ ወጣቶች ገቢያቸውን ከ280 ሺህ ብር ማሳደግ እንደቻሉም ተናግረዋል።

በወረዳው ሶስት ማዕከላት ከ120 በላይ ኢንተርፕራይዞች በተደራጁበት ሥራ ዉጤታማ እንዲሆኑ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን በሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ፅህፈት ቤት የከተሞች አቅም ማስፈፀም ሥራ ቡድን መሪ አቶ አያሌው ላሎ አስረድተዋል ።

ቀጣይነት ያለው የሥራ ፈጠራ ዕድሎችን ለማስፋፋት የብድር አስመላሽ ግብረሀይል በማደራጀት በተከናወኑ ተግባራት ከ2 ሚሊዮን 6 መቶ ሺህ ብር በላይ ብድር ማስመለስ መቻሉን ቡድን መሪው ተናግረዋል ።

ባለፈው በጀት ዓመት በተለያዩ ሥራ መስኮች ለተሠማሩ ወጣቶች ማህበራት ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ መሠራጨቱም ተገልጿል ።

ዘጋቢ፡ ዳኜ ጥላሁን – ከጂንካ ጣቢያችን