የዜጎችን የዳበረና ጠንካራ የስራ ባህል በማሳደግ ተጠቃሚነታቸዉን በዘላቂነት ለማረጋገጥ እተየሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ጥቅምት 06/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የዜጎችን የዳበረና ጠንካራ የስራ ባህል በማሳደግ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነታቸውን በዘላቂነት ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ገለፀ።
ቢሮዉ በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት 3 ወራት የተከናወኑ ተግባራት ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ በሰጡት መግለጫ እንደገለፁት ቢሮዉ በክልሉ በሁሉም አከባቢዎች ስራ ፈላጊዎችን በመለየት፣ ስልጠናዎችን በመስጠትና አደራጅቶ ወደ ስራ እንዲገቡ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በ2017 በጀት አመት በክልሉ ለ350 ሺህ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው ባለፉት 3 ወራት በርካታ ዜጎችን የአገር ዉስጥ እና የዉጭ ስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ መቻሉን ሀላፊዉ ገልፀዋል።
በዚህም የዜጎች የስራ ባህል በማሳደግ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነታቸዉን በዘላቂነት ለማረጋገጥ እተሰራ እንደሚገኝ አቶ ሙስጠፋ ገልፀዋል።
የክልሉ ዜጎች የእለት ጉርስ ከመቻል ባለፈ ሀብት በመፍጠር እንደ አገር አምራችና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከፌደራል ጀምሮ በየደረጃዉ ከሚገኙ መዋቅሮች ጋር በመቀናጀት አጫጭር የክህሎት ስልጠናዎች እየሰጠ ይገኛል ብለዋል፡፡
ስራ ፈላጊዎች የግብአት አቅርቦት አገልግሎት እንዲያገኙ ከሚመለከታቸዉ ባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ጨምረው አብራርተዋል፡፡
ክልሉ በተያዘዉ በጀት አመት ለስራ እድል ተጠቃሚዎች 50 ሚሊዮን ብር መመደቡን ሀላፊዉ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ የተመደበዉ በጀት ለስራ እድል ፈጠራ በቂ ባለመሆኑ ከ2005 ዓም ጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ተወዝፈዉ የቀሩ የመንግስት እዳዎችን ለማስመለስ ቢሮዉ በአፅኖት ይሰራል ብለዋል። ለዚህም ግብረ-ሀይል መቋቋሙን አክለዋል፡፡
ጠንካራ ተቋም በመገንባት፣ ዘላቂ የስራ እድል በመፍጠር እና የኢንተርፕራይዝ ልማት በማደራጀት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ቢሮዉ በሚቀጥሉት ጊዜያት በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።
በተለይም የዜጎች የዉጭ አገር የስራ ስምሪት ከፍላጎት አንፃር የተመጣጠነ እንዲሆን ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራልም ብለዋል።
ዘጋቢ፡ ሪያድ ሙህዲን – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ