የምግብ ዋስትናን በሚያረጋግጡ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ እንደሚገኝ በሀዲያ ዞን የሌሞ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት አስታወቀ
በወረዳው ሹርሞ ዳጮ ቀበሌ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ዘርፍ የተሠማራው “መሠረት አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ማህበር” የአካባቢውን ገበያ ከማረጋጋት አንጻር ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።
የማህበሩ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አርሶአደር መሠረት ጌታቸው እንደገለፀችው፤ በአካባቢው ሴቶች ዘንድ እምብዛም ወዳልተለመደው የእርሻ ስራ ላይ መሰማራቴ በዘርፉ የሚስተዋለውን የምርት እጥረት በመቅረፍ የድርሻዬን ለማበርከትና ስራ ፍለጋ በህገወጥ መንገድ ለሚሰደዱ ወንድም እህቶቼ እዚሁ ሰርተው መለወጥ እንደሚቻል ለማስገንዘብ ነው።
በወረዳው ከተጀመረው ስምንት አመታትን ያስቆጠረው “የመሠረት አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ማህበር” ጅምር ላይ በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ የጀመረውን የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በማስፋፋት አሁን ላይ እስከ 50 ሄክታር በማድረስ ለተጠቃሚው ህብረተሰብ ጥሩ አማራጭ ሆኖ መቅረቡን ገልጻለች።
በስራው ወቅት በርካታ ትዕግስትን የሚፈታተኑና ቁርጠኝነትን የሚጠይቁ አጋጣሚዎችን በትግል ማለፍ ችያለሁ የምትለን አርሶአደር መሠረት፤ ሳይሰለቹና ተስፋ ሳይቆርጡ መስራት ለስኬት የሚያበቃ እንደሆነም የግሏን ተሞክሮ አጋርታናለች።
“ነገሮች ሁሉ በገንዘብ ይገዛሉ፤ ጊዜ ግን በምንም አይገዛም” የምትለው ወ/ሮ መሠረት፤ ወጣቱ ትውልድ ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም የተሻለ ኑሮ ለመምራትና እራሱንና አካባቢውን ለመለወጥ ስራን ሳያማርጥ መስራት እንደሚጠበቅበትም አስተያየቷን ሰጥታለች።
አሁን ላይ በስራዋ ውጤታማ በመሆኗ ከራሷ አልፋ ለአካባቢው ማህበረሰብ መድረስ መቻሏን በመግለጽ ይበልጥ ውጤታማ ለመሆንና ዘርፉንም ለማስፋፋት የምርት መሸጫ ቦታና የእርሻ ማሽነሪ ድጋፍ ከመንግስት በኩል እንድመቻችላትም ጠይቃለች።
አቶ ሳሙኤል ሀብቴ የወ/ሮ መሠረት ባለቤትና የማህበሩ ስራ አስተባባሪ ሲሆን በስራ ወቅት የሚፈጠረውን ኪሳራንና ድካምን ተቋቁሞ ለስኬት መብቃትን ከአርሶአደር መሠረት ህይወት መማር እንደሚቻል ተናግሯል።
ሴቶች ትክክለኛ ድጋፍ ካገኙ የትኛውንም ስራ በውጤታማነት የመስራት አቅም አላቸው የሚለው አቶ ሳሙል እሱም በመደበኛነት ከምሰራው ከመንግስት ስራ ጎን ለጎን የማህበሩን ስራ በማገዝ ለጋራ ዕድገት የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ አስረድቷል።
በዚሁ ማህበር የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወጣቶችም ሰርተው በሚያገኙት ገቢ ኑሯቸውን ከመምራትም ባሻገር በቀጣይ የራሳቸውን የስራ ዘርፍ ፈጥረው ለሌሎች ለመትረፍ እየሰሩና በዚህም ደስተኞች ስለመሆናቸው ተናግረዋል።
የሌሞ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሰልፋሞ ወ/ዮሐንስ በበኩላቸው ወረዳው የምግብ ዋስትናን በሚያረጋግጡ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ እንደሚገኝ ገልፀው ከጓሮ ልማት ጀምሮ እስከ አምራች ደረጃ የሚንቀሳቀሱ አርሶአደሮችን የመደገፍ ስራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በወረዳ ደረጃ በርካታ የስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፎች ስለመኖራቸው ያመላከቱት ኃላፊው የወ/ሮ መሠረት “የአትክልትና ፍራፍሬ አምራች ማህበር”ም አንዱና የአካባቢውን ገበያ ከማረጋጋት አኳያ ጉልህ አበርክቶ ያለው ነው ብለዋል።
ከመሸጫ ቦታና ከእርሻ ማሽነሪ አቅርቦታ እንዲሁም ከማስፋፊያ ቦታ ዝግጅት ጋር ተያይዞ ጽ/ቤቱ ከሌሎች ባለድርሻ መስሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር ለመፍታት እንደሚሰራ ያስረዱት አቶ ሰልፋሞ፤ ሌሎችም ወጣቶችና ስራ ፈላጊ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የአርሶአደር መሠረትን ተሞክሮ በመጋራት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ዘጋቢ: አለቃል ደስታ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ