ሰንደቅ አላማ የነጻነታችንና የሉአላዊነታችን መገለጫና ለህዝቦች ህብረት ከፍ ያለ ምልክት በመሆኑ ሁሉም የሚገባውን ክብር ሊሰጠው እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 04/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሰንደቅ አላማ የነጻነታችንና የሉአላዊነታችን መገለጫና ለህዝቦች ህብረት ከፍ ያለ ምልክት በመሆኑ ሁሉም የሚገባውን ክብር መስጠት እንዳለበት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አሳሰበ።

ሰንደቅ አላማችን ለብሄራዊ አንድነታችን ለሉአላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ በሚል መሪ ቃል 17ኛው የሰንደቅ አላማ ቀን በአርባምንጭ ከተማ በደመቀ መልኩ ተከብሯል።

ሰንደቅ አላማችን የስራ፣ የልምላሜ፣ የእድገት ምልክት፣ የተስፋ፣ የፍትህና የእኩልነት ማረጋገጫ የመስዋእትነትና የጀግንነት ማሳያ በመሆኑ ለ17ኛ ጊዜ በአርባምንጭ ከተማ የሚገኙ የክልል የዞን የከተማ አመራሮችና የመንግስት ሰራተኞች በተገኙበት በደመቀ መልኩ እየተከበረ ይገኛል።

የጋሞ ዞን የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ መኮንን ሞገስ የሰንደቅ አላማችን የሉአላዊነታችን መገለጫ የአንድነታችን ማሳያ በመሆኑ ክብር ልንሰጠዉና ልንጠብቀው ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የሁሉም ሀይማኖት፣ ባህል፣ ታሪክ የተነቀሰባት ባለብዙ ጸጋ ባለቤት መሆኗን በመገንዘብ ሁሉም ለጋራ ልማትና አላማ  በመቆም ኢትዮጵያን ማጽናት ያስፈልጋል ብለዋል አቶ መኮንን።

በበአሉ አከባበር ላይ የተገኙት የእለቱ የክብር እንግዳ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት የግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር ቋሚ ኮሚቴ ሰብስቢ አቶ ጠንክር ጠንካ እንደተናገሩት ሰንደቅ አላማ የአንድ ሀገር መለያ ብቻ ሳይሆን የነጻነታችንና የሉአላዊነታችን መገለጫ ለህዝቦች ህብረት ከፍ ያለ ምልክት በመሆኑ ሁሉም የሚገባውን ክብር መስጠት ይገባዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የምትሻገር ሀገር ሆና በማይሻገሩ ጎታች አስተሳሰቦች ወደ ኋላ መቅረት የለባትም የሚሉት አቶ ጠንክር የልዩነት ትርክቶችን በማስወገድ ለኢትዮጵያ አንድነት ዘብ ልንቆም ይገባል ብለዋል።

ህልማችን የልዕልና በመሆኑ በዚህ ልዕልና መር ህልማችን ችግሮቻችንን ከመቅረፍ ባለፈ ነቅለን በመጣል ያሉንን ጸጋዎች ለይቶ በማወቅና ወደ ተግባር በመቀየር ኢትዮጵያን የበለጸገች እንድትሆንና ሰንደቋ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ልናደርግ ይገባል ብለዋል።

የክልሉ ምክር ቤት ጽ/ቤት ሀላፊ ወ/ሮ ተስፋነሽ ጥላሁን በበኩላቸው ሰንደቅ አላማችን የሉአላዊነት መገለጫ በመሆኑ አባቶቻችን ያስቀመጡልንን በመሰዋእትነት የተገኘ ውጤት በልማቱ ማስቀጠል የኛ ድርሻ ነው በማለት ተናግረዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ምልክትና የአንድነት አርማ የሆነው ሰንደቅ አላማችን በሁሉም መስክ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ማድረግ ከሁሉም እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን