የማዕከሉ ተመራማሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በጉራጌ ዞን በቸሃና ጉመር ወረዳዎች በኩታ ገጠም አመራረት ዘዴ የለማውን የጤፍና ስንዴ ሰብል ማሳ የመስክ ጉብኝት አካሂደዋል።
በዕለቱ በክብር እንግድነት የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ተወካይ አቶ ደምሴ ማርቆስ እንደገለፁት፤ በክልሉ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ እየተሰራ ሲሆን ይህንን ለማሳካት ደግሞ ከግብርና ምርምር ማዕከላት ጋር ተቀናጅቶ መስራት ወሳኝ እንደሆነ አንስተዋል።
በዕለቱ በምርምር ማዕከሉ ድጋፍ የለማው የጤፍና ስንዴ ሰብል ማሳ አሁን ላይ ሲታይ የተሻለ ምርት እንደሚገኝበት የሚያመላክት መሆኑን ጠቁመው ይህ ተግባር ወደፊትም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
የቸሃ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ መህሙድ በመስክ ጉብኝተ ወቅት እንደገፁት የምርምር ማዕከሉ የግብርና ልማት ዘርፍ ውጤታማነትን ለማረጋገጥ እያደረገ ባለው ጥረት አርሶ አደሩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና የተሻሻሉ ዝርያዎችን ተጠቅሞ ምርትና ምርታማነቱን ማሳደግ እንዲችል በተቀናጀ መልኩ በመስራት እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ቢላል ተማም በበኩላቸው ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት በሰብል፣ በተፈጥሮ፣ በእንስሳት፣ በግብርና ኢኮኖሚክስ ስርዓት፣ ጾታ ምርምርና ሌሎችም ዘርፎች እየሰራ ሲሆን በተለይ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት የሚያሳድጉ ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በግብርና ቴክኖሎጂ ሽግግርና ኮሙኒኬሽን በምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ገንዘብ ድጋፍ በቸሃና ጉመር ከ42 ሄክታር በላይ ማሳ በጤፍና ስንዴ ኩታ ገጠም የማምረት ቴክኖሎጂ የማስተዋወቅ ሥራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው የመስክ ጉብኝቱም ዓላማ እነዚህን ምርጥ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ወደሌሎች አካባቢዎች ለማስፋትና ተደራሽ ለማድረግ ታስቦ እንደሆነ ገልጸዋል።
በምርምር የተገኙ የግብርና ዝርያዎችን በተመረጡ የአርሶ አደር ማሳዎች ላይ ሙከራ በማድረግ ውጤታማ መሆናቸው ተረጋግጦ ወደሌሎች አካባቢዎች ተደራሽ የማድረግ ስራዎች እየተሰሩ ስለመሆናቸው የተናገሩት ደግሞ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግብርና ቴክኖሎጂ ሽግግርና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዲላሞ አዲላ ናቸው።
በቸሃና ጉመር ወረዳዎች የለማው የጤፍና ስንዴ ኩታ ገጠም ማሳ አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልፀው የስንዴ ሰብል መሬቱን ለየት የሚያደርገው ቀደም ሲል ለጎርፍ የተጋለጠ በመሆኑ ጠረጴዛማ እርከን በመስራትና አሲዳማነቱን በኖራ በማከም አሁን ላይ ለተሻለ ውጤት ማብቃት መቻሉን ጠቁመዋል።
ጉብኝቱ በተደረገባቸው ቀበሌያት የሚገኙ አርሶ አደሮች በሰጡት አስተያየት የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል ያደረገላቸዉ የምርጥ ዘርና ግብዓት አቅርቦት ድጋፍ ለምርታማነታቸው ከፍተኛ እገዛ እንዳደረገላቸው ገልፀዋል።
ዘጋቢ: ናስር ጀማል – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ