የጉራጊኛ ቋንቋን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትኩረት መስራት እንዳለባቸው የጉራጌ ዞን አስተዳደር አሳሰበ

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ የጉራጊኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት የፊደል ገበታና የትምህርት አሰጣጥ በተመለከተ በወልቂጤ ከተማ ለ2 ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ የነበረው የአሰልጣኞች ስልጠና ተጠናቋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በመድረኩ ተገኝተው እንዳሉት፤ ቋንቋ የማንነት መገለጫ መሆኑን ጠቅሰው ካለፉት ሁለት አመታት ወዲህ በዘርፉ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

ጉራጌ በርካታ ባህል፣ ወግና ሌሎችም እሴቶች እንዳሉት ያነሱት አቶ ላጫ የጉራጊኛ ቋንቋ ከመጥፋት በመታደግ እንዲያንሰራራ ለማድረግ በዞኑ ለዘርፉ ውጤታማነት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

አክለውም ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆን አስፈላጊውን በጀት በመመደብ የጉራጊኛ መጽሀፍት የማሳተምና ስልጠናዎች የመስጠት ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኝ ጠቁመው ከ1 ሺህ 2 መቶ በላይ የጉራጊኛ ቋንቋ መምህራን መለየታቸውን አብራርዋል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ተወካይ እና የመምህራን ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ባቂ በሰማ በበኩላቸው ቋንቋ የሚለማው በትምህርት ስርዓት ውስጥ ተቀርጾ ለዜጎች ትምህርት ሲሰጥበት፣ በኪነ ጥበብና በሚዲያ ቋንቋ ማህበረሰቡ ሲገለገልበት ነው ብለዋል።

የጉራጊኛ ቋንቋ ከዚህ ቀደም የትምህርት እና የሚዲያ ቋንቋ እንዲሆን አልተሰራም ያሉት አቶ ባቂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቋንቋውን ለማልማት የተጀመሩ ስራዎች ቢኖሩም አሁንም ሰፊ ውስንነቶች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡

ይህም ቋንቋው በተፈለገው ልክ እንዳይለማ እንዳደረገውም በመጥቀስ፤ ይሁን እንጂ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በተደረገው ጥረት ባለፉት ዓመታት በቅድመ 1ኛ ደረጃ ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ሲማሩ መቆየታቸውን ገልፀዋል።

በዘንድሮ አመትም የ2ኛ ክፍል የጉራጊኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋ የመጽሀፍ ዝግጅት ተጠናቆ የሙከራ ትግበራ መጀመሩንም ተናግረዋል።

አክለውም በ2017 የትምህርት ዘመን በ9 መቶ 31 ቅድመ አንደኛ ሙሉ የትምህርት አይነት፣ በ4 መቶ 31 ቅድመ አንደኛ ክፍል ሙሉ ትግበራ እና በ2ኛ ክፍል በ18 ትምህርት ቤቶች የሙከራ ትግበራ ማስጀመር መቻሉን ገልጸዋል።

ስልጠናውም ለመማሪያነት የተዘጋጁ የጉራጊኛ መጽሀፍት ለመምህራን እና ለሌሎች ለሚመለከታቸው አካላት በማስተዋወቅ እንዲሁም የመማር ማስተማሩ ስነ-ዘዴ ላይ ስልጠና የተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

ስልጠናው በወሰዱ 1 መቶ 20 መምህራን ከ1 ሺ 2 መቶ 50 በላይ ስልጠናውን ያልወሰዱ መምህራንን ለማሰልጠን ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ቋንቋው የበለጠ እንዲለማና የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እንዲሁም በዘርፋ ያሉ ውስንነቶችን ለመቅረፍ ባለድርሻ አካላት እንዲያግዙም አቶ ባቂ ጠይቀዋል፡፡

የዞኑ ባህልና ቱሪዝም የቋንቋና ስነ-ጽሁፍ ቡድን መሪ አቶ ባህሩ ሊላጋ እንዳሉት ቋንቋው የበለጠ እንዲያንሰራራና እንዲያድግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን በመግለፅ ይህም በህብረተሰቡና በመንግስት በኩል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ነው ያሉት።

ስልጠናውን ከወሰዱ ሰልጣኞች መካከል መ/ርት ታሪኳ መልስ እና መ/ር ዋቢ ያሲን በሰጡት አስተያየት በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመማር ማስተማር ሂደቱ ከጊዜ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቅሰው ቀጣይ ተከታታይ ሙያዊ እገዛዎች ቢኖሩ የበለጠ እንድንሰራ ያደርጋል ብለዋል።

ጨምረውም ልጆች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመማር መብታቸው መጠበቅ እንዳለበት አንስተው ከግብአት አኳያ ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን ጥረት ማድረግ አለበት ብለዋል።

ዘጋቢ፡ ዝናሽ ሙሉጌታ – ከወልቂጤ ጣቢያችን